ሳላስበው ከፈጸምኩት ተግባር ብዙ የተማርኩበት አጋጣሚ
- Jun 19, 2015
- 2 min read
Updated: Jan 11
ጊዜው በአገራችን አቆጣጠር በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ሥፍራው በስዊዘርላንድ ዙሪክ፡፡ አርብ ዕለት እንደወትሮዬ በማለዳ ተነሥቼ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡ ከወትሮው የተለየ ነገር ይገጥመኛል የሚል ጥርጣሬውም አልነበረኝም፡፡ ረፋዱ ላይ ከምሠራበት ክፍል ሆኜ ቁልቁል በመስኮት ወደ ውጭ ስመለከት ሁለት በመሥሪያ ቤቱ ያልተለመዱ እንግዳ ሰዎችን ተመለከትኩ፡፡ ውስጤ የሆነ ነገር ሽብር ቢልብኝም ብዙም ቁም ነገር ሳልለው ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፡፡ ሳይዘገይ በመስኮት የተመለከትኳቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኜ ወደ ምሠራበት ክፍል ዘልቀው ስሜን ከነአባቴ ጠሩኝ፡፡ አቤት ብዬ ወደ እነርሱ ቀረብኩ፡፡ ፖሊስ መሆናቸውን ከነገሩኝ በኋላ መታወቂያዬን እንዳሳያቸው ጠየቁኝ፡፡ አሳየኋቸው፡፡ ካመሰገኑኝ በኋላ በደሞዝ ተቀጥሬ የመሥራት ፈቃድ ያለኝ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ የለኝም በድብቅ ነው የምሠራው፡፡ ዝም አልኳቸው፡፡ ወደፖሊስ ጣቢያ አብሬያቸው መሄድ እንደሚገባኝ ነገሩኝ፡፡ ምርጫ አልነበረኝም አብሬያቸው ባዘጋጁልኝ መኪና ሄድኩኝ፡፡
ጣቢያ እንደደረስኩኝ የፈጸምኩት በሀገሩ ሕግ የሚያስቀጣኝ ተግባር መሆኑን አሳወቁኝ፡፡ አሰቀድሜም አውቀው ስለነበር አዲስ አልሆነብኝም፡፡ ከዚያ በኋላ በሕግ አግባብ ሊያግዘኝ የሚችል ሰው ይኖር እንደሆነና ስልክ መደወል እፈልግ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ እኔም እንደምፈልግ ነግሬያቸው ተፈቀደልኝ፡፡ ነገር ግን የደወልኩለት ሰው በቅርብ የሌለ በመሆኑ ዛሬ በዛሬ ሊደርስልኝ እንደማይችል ከይቅርታ ጋር አሳወቀኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ ዐርብ በመሆኑ ቅዳሜን እና ዕሁድን ጨምሮ በፖሊስ ጣቢያ ማሳለፍ እንደሚኖርብኝ ተነገረኝ፡፡
ወደ አንድ አነስተኝ ክፍል ከተወሰድኩ በኋላ ቅድም ከምሠራበት ቦታ በመኪና ይዘውኝ ከመጡት ፖሊሶች አንዱ በፖሊስ ጣቢያው ለሦስት ቀናት መቆየቴ እርግጥ ስለሆነ አንዳንድ በኪሴ የሚገኙ እና ወደ እስር ቤት ይዞ ለመግባት በሕግ የተከለከሉ አልባሳቶቼን እንዳስረክበው ጠየቀኝ፡፡ ዋሌቴን፣ ተንቀሳቃሽ ስልኬን፣ በኪሴ የነበሩ ጥሬ ብሮችን፣ ቀበቶዬን እና የመሳሰሉትን ሰጠሁት፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር በሕወቴ ትልቅ ትምህርት የተማርኩበት አጋጣሚ የተፈጠረው፡፡ እንዲህ ነው ነገሩ፡፡ አለኝ ብዬ የማስበውን ቁሳቁስ ሁሉ አስረክቤ ከጨረስኩኝ በኋላ አንገቴ ላይ ሀብል አድርጌ እንደሆነ ጠየቀኝ፡፡ አላደረኩም ነበር፡፡ ከዚያ የጋብቻ ቀለበቴን ተመለከተ እና በጭንቅላቱ ምልክት ሰጠኝ፡፡ አውልቀው ማለቱ ነው፡፡ የጋብቻ ቀለበት ነው አልኩት፡፡ አውቃለሁ አለኝ፡፡ ሁኔታውን ሳየው እንደማይለቀኝ ገባኝ፡፡ ሃይማኖታዊ መሆኑን እና በምንም ምክንያት ከጣቴ ላይ ማውለቅ እንደማይገባኝ ይህ ደግሞ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሆኑን አስረዳሁት፡፡ ሊቀበለኝ አልፈለገም፡፡ ከዚያ ለማውለቅ ሞከርኩ፡፡ በጋብቻዬ ዕለት ባለቤቴ ካጠለቀችልኝ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ከጣቴ ወልቆ አያውቅም፡፡ ውስጤ ባጣም ተሸበረ፡፡ የሆነ ከባድ ነገር የምፈጽም መስሎ ተሰማኝ፡፡ ድንገት ግን ወደ ፖሊሱ ዞሬ ይህንን ቀለበት እዚህ ጣቴ ላይ ያጠለኩት እኔ አይደለሁም ባለቤቴ ናት ያጠለቀችልኝ፡፡ እርሷ ደግሞ እጅቅ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ነው በቃልኪዳን ያጠለቀችልኝ አልኩት፡፡ ስለዚህ ይቅርታ አድርግልኝ እኔ የማውለቅ መብቱም ሆነ ሥልጣኑ የለኝም፡፡ ላለመታዘዝ ፈልጌ አይደለም ከፈለክ እንካ አንተ ራስህ አውልቅና ውሰደው፡፡ አልኩና እጄን ዘረጋሁለት፡፡ አታምኑኝም ደነገጠ ሸሸኝ፡፡ ሁኔታውን ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስታውሰው በሆነ ነገር ልወጋው የሰነዘርኩ ነበር የሚመሰለው፡፡ አንድ ጊዜ አለኝና ተነስቶ ወደ ሌላ ክፍል ትቶኝ ሄደ፡፡ ተመልሶ መጣና ወርቅ ነው? ብሎ ጠየቀኝ፡፡ አዎን አልኩት ተመልሶ ወጣና ትንሽ ቆይቶ ተመልሶ መጣና አድርጌው ልገባ እንደምችል ነገረኝ፡፡
አድርጌው ገባሁ በዚያን ወቅት በእስር ቤቱ ውስጥ ከነበሩ እስረኞች ሁሉ የጣት ቀለበት አድርጌ እንድገባ የተፈቀደልኝ ብቸኛ እስረኛ እኔ ነበርኩ፡፡ በርካታ እስረኞች አስረክበው እንዲገቡ የተጠየቁ በመሆኑ የእኔ ጣት ላይ ቀለበቴን ሲመለከቱ እንዴት እንዳልተቀበሉኝ ጠየቁኝ፡፡ በጌታ ሥራ ተገረምኩኝ፡፡
ግን ግን የጋብቻ ቀለበታችንን በጣታችን ላይ ያጠለቅነው እኛ እንዳልሆንን እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን እኛ የማውለቅ መብቱም ሆነ ሥልጣኑ እንደሌለን ስንቶቻችን ይሆን ልብ የምንለው፡፡ እውነቴን ነው እኔ በዛን ወቅት ከፖሊሱ ጋራ እያወራሁ እንኳን ይህ ዓይነቱ ስሜት እና ግንዛቤ አልነበረኝም፡፡ እንደው ስለመጣልኝ ነው እንደዛ ያልኩት፡፡ በእርግጥ ማውለቁ በጣም ከብዶኝ ነበር፡፡ ግን አሁን በምነግራችሁ መልኩ አልተረዳሁትም ነበር፡፡ ወገኖቼ እውነት ልንገራችሁ በጣታችን ላይ ያጠለቅነው ይህ ቀለበት በተቀደሰው የእግዚአብሔር መንበር እና ጉባኤ ፊት የገባነው ቃል ኪዳን ምልክት ነው፡፡ ስለዚ በማናቸውም ሁኔታ እንደ ቀላል ልናወልቀው አንችልም ያጠለቅነው እኛ አይደለንም የእኛ ጥሪ እና ኃላፊነት ቀለበቱን ከጣታችን እንዳይወልቅ መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማረውና ክቡር አባ ገብረማርያም የጋብቻ ቀለበታችን ወይ ይመሰክርልናል ወይ ይመሰክርብናል ይሉ ነበር፡፡





Comments