top of page

ጋብቻ የማይፈርስ ቃልኪዳን

  • Jan 14
  • 1 min read

ይህ ጽሑፍ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ (Catechism of the Catholic Church - CCC 1601-1666) ላይ በመመስረት ስለ ምስጢረ ተክሊል የተዘጋጀ አጭር ማብራሪያ ነው።


ጋብቻ (ምሥጢረ ተክሊል) በፈጣሪ ፈቃድ የተመሰረተ፣ በወንድና በሴት መካከል የሚደረግ የህይወትና የፍቅር አንድነት ነው። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በፍቅር ስለሆነ፣ ለፍቅርም ጠርቶታል። ጋብቻ በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ የታተመ የፍቅር ጥሪ ነው። ካቴኪዝም እንደሚያስተምረው ጋብቻ ውል ሳይሆን ቅዱስ "ምስጢር" (Sacrament) ነው። ይህም ማለት ባልና ሚስት በጋብቻቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን ጸጋ ይቀበላሉ ማለት ነው። ጋብቻ የሁለት ሰዎች ስምምነት ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የሚገኝበት ቅዱስ ጥምረት ነው። ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው እንዲቀደሱና ዓለምን በቅድስና እንዲሞሉ የተሰጠ ጸጋ ነው። ጋብቻ ሁለት ዋና ዋና ግቦች አሉት። እነሱም የባልና ሚስት አንድነት (የእርስ በርስ መረዳዳትና ፍቅር)፣ ልጆችን መውለድና ማሳደግ ናቸው።

ምሥጢረ ተክሊል የባልና የሚስት ነጻ ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት የሚከተሉትን ነጥቦች ማካተት አለበት፦

  • ነጻ ፈቃድ፦ ማንም ሳይገፋፋቸው በገዛ ፈቃዳቸው መወሰን አለባቸው።

  • ለዘለዓለም መጽናት፦ "ሞት እስኪለየን ድረስ" የሚለው ቃል በምንም ሁኔታዎች የማይፈርስ አንድነትን መሆኑን መረዳት። ቤተክርስቲያን በቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት መሠረት "እግአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው" (ማቴ 19:6) በማለት የጋብቻን የማይፈርስ ባህሪ ታስተምራለች። ይህ አንድነት ለባልና ሚስት ጥበቃና ለልጆች ደህንነት ወሳኝ ነው።

  • ታማኝነት፦ ለአንድ የትዳር አጋር ብቻ ታማኝ መሆን።

ባልና ሚስት ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ያለውን ፍቅር በኑሯቸው እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል። ካቴኪዝም ክርስቲያን ቤተሰብን "የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያን" ብሎ ይጠራዋል። እምነት፣ ጸሎትና በጎ ምግባር መጀመሪያ የሚቀሰሙት በቤተሰብ ውስጥ ነው። ልጆች ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትንና ይቅርታን መጀመሪያ የሚማሩት በቤተሰብ ውስጥ ነው። የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ ደግሞ ጋብቻንና ቤተሰብን “የማኅበረሰብ ሕያው ሕዋስ” (The original cell of social life) በማለት ይጠራቸዋል። ቤተሰብ ሕፃናት፣ አረጋውያንና ሕመምተኞች እንክብካቤ የሚያገኙበት የመጀመሪያው ቦታ ነው። ጠንካራ ቤተሰብ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሰላምና ፍትሕ ይሰፍናል። ቤተሰብ ሲዳከም ግን ማኅበረሰቡ ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ይጋለጣል።




 
 
 

Comments


bottom of page