አለመግባባታችንንም ቢሆን ለትዳራችን እድገት ማዋል እንችላለን
- Jun 17, 2016
- 2 min read
Updated: Jan 11

ባልና ሚስት በመካከላቸው አለመግባባት ሳይከሰት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ በኑሯቸው ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች መጋጨት እና መጣላት ያጋጥሟቸዋል፡፡ ነገር ግን አለመግባባት በሚከሰት ጊዜ ፍትሐዊ እና ለፍቅራችሁ ገንቢ በሆነ መልኩ መወጣት ይቻላል፡፡ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ጠቃሚ ሃሳቦች ብታነቧቸው ይጠቅሟችኋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ አለመግባባቶች የሚካረሩት በአሸናፊነት ሥነልቦና የሚመሩ በመሆኑ ነው፡፡ የመነጋገራችሁ ዋና ዓላማ እርሷን ወደ አንተ ወይም አንተን ወደ እርሷ ሃሳብ ለመውሰድ የሚደረግ ትግል መሆን የለበትም፡፡ ይልቅስ ሁለታችሁንም ከዚህ በፊት ወደ አልነበራችሁበት አንድ አዲስ ምእራፍ የሚያሸጋግር እንጂ፡፡ በመሆኑም ሁለታችሁም በእኩል ደረጃ እየተደማመጣችሁ መነጋገር አለባችሁ እንጂ ውይይታችሁ በማእረግ ተዋረድ አካሄድ መሠረት መከናወን የለበትም፡፡ ይህም ማለት አንዱን ባለሥልጣን ሌላውን የበታች፣ አንዱን ተናጋሪ ሌላውን ተቀባይ፣ አንዱን አዛዥ ሌላውን ታዛዥ የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡
የንግግራችሁ ውጤት ምን ሊመስል እንደሚገባው ወስናችሁ አትነጋገሩ፡፡ መጨረሻውን ወስናችሁ በገባችሁበት ውይይት ውስጥ ጊዜ ማጥፋታችሁ ለሁለታችሁም የሚበጅ አይደለም፡፡ እናንተ ትክክል እንደሆናችሁ በማመን የሌላኛውን ሰው ሃሳብ ለማስቀየር ከሆነ የምትጥሩት አለመግባባቱ ይካረራል እንጂ ገንቢ ውጤት አታመጡም፡፡ የምታደርጉት ውይይት በሁለታችሁም አመለካከት ላይ ለውጥ የሚያመጣ እና አዲስ ግን የጋራ ወደ ሆነ ድምዳሜ እንድትደርሱ የሚረዳችሁ መሆን አለበት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደጠቃሚ ድምዳሜ እንዲመራችሁ አስቀድመችሁ ጸልያችሁ ወደውይይታችሁ ግቡ፡፡
እንደ አንድ ጠቃሚ ነጥብ ልጠቁማችሁ ከኑሮ አጋራችሁ ጋር አለመግባባት ተከስቶ በምትነጋገሩበት ጊዜ እርሱ/ሷ ከሚናገራቸው/ከምትናገራቸው ነገሮች ውስጥ እናንተ ልትስማሙባቸው የምትችሏቸውን ነጥቦች ፈልጉና አውጡ፡፡ ይህ/ህች ሰው ከሚናገረው/ከምትናገረው ነገር ውስጥ እኔ ልስማማበት የምችለው ነጥብ የቱ ነው? ራሳችሁን ጠይቁ፤ ከእርሱ/ሷ ንግግር ውስጥ ትክክል መሆኑን የማልክደው ነገር የቱ ነው? አስቡ፤ በሚናገረው ወይም በምትናገረው ነገር ውስጥ ምንም እውነት የሆነ ነገር የለውም? እኔም እውነት እንደሆነ የማምንበት ነገር የቱ ነው? በታማኝነት እና በቀና ልቦና መርምሩ፡፡
እጅግ የከፋ ጸብ የሚፈጠረው የኑሮ አጋራችሁ የተሳሳተ/ች መሆኑን/ኗን ብቻ እንጂ ከዚያ የተለየ አስተሳሰብ ለማሰብ ለራሳችሁ ዕድል ሳትሰጡት/ጧት ስትቀሩ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በመካከላችሁ ፈጽሞ መቀራረብ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ እስኪ አስቡት “የቱ ጋ ነው እስኪ ባለቤቴ ትክክል የሆነው/ችው?” “እርሱ/ሷ ከሚናገረው/ከምትናገረው ውስጥ እኔም የማምንበት ነጥብ የቱ ነው?” “እውነት መሆኑን እኔም የማልክደው የቱ ነው?” ብላችሁ እነዚህን ነጥቦች አንጥራችሁ ማውጣት ስትችሉ አለመግባባታችሁ እንዴት መልኩን ሊቀይር እንደሚችል አይታያችሁም፡፡ ይህን ማድረግ ከቻላችሁ ራሳችሁን በብዙ ነገር ታግዛላችሁ፡፡
በመጀመሪያ ስህተት የሆነውን ለመፈለግ ከምታባክኑት ኃይል ይልቅ ትክክለኛ ነገርን እና እውነትን ለመፈለግ እየጣራችሁ መሆኑ በራሱ በውስጣችሁ መልካም አመለካከትን በመፍጠር አዎንታዊ ስሜት እንዲኖራችሁ ያደርጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በኑሮ አጋራችሁ አመለካከት ውስጥ የሚገኙ እውነታዎችን ለመፈለግ የምታደርጉት ጥረት የኑሮ አጋራችሁን አመለካከት ይቀይረዋል፡፡ የበለጠ አዎንታዊ አመለካከት እንዲረው/ራት ያደርገዋል/ጋታል፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉ የአለመግባባቱን አቅጣጫ ይቀለብሰዋል ማለት ነው፡፡
በባልና ሚስት መካከል አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ ማስወገድ ያለባቸው ነገር ቢኖር ሁለት የተለያዩ ጉዳዮችን ይዘው ግራ ቀኝ ቆመው እንደሚሟገቱ እንደ ሕግ ጠበቆች የሚመስል ክርክር ማድረግን ነው፡፡ እርስ በእርስ መደማመጥ የሌለበት በሕግ እና በአንቀፆች ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሟገት አስተሳሰብ ወደ መፍትሔ ሊመራ አይችልም፡፡ ጠበቆች ተቃራኒ ተሟጋቻቸው ትክክል እንደሆነ ቢያውቁ እንኳን የደምበኛቸውን ሃሳብ ደግፈው እስከ መጨረሻ ይሟገታሉ፡፡ የደምበኛቸው ሃሳብ ሊያሸንፍ የሚችልበትን አማራጭ በመፈለግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ የእነርሱ ግብ የሃሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እና መደገፍ ሳይሆን የቆሙለት የሞያውን ሥነምግባር ተከትለው የደምበኛቸው ሃሳብ እንዲያሸንፍ እና እነርሱ ገንዘባቸውን እንዲቀበሉ ማድረግ ነው፡፡
ከዚህ በተለየ አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ የሚገኘውን እውነታ ለመረዳት ጥረት የሚያደርጉ ባልና ሚስት ግን ኢየሱስ ክርስቶስን በኑሮ አጋራቸው ሕይወት ውስጥ ለማየት የሚያስችላቸውን እርምጃ አንድ ብለው የተራመዱ ናቸው፡፡ ይህንን በሕወታችሁ እየተለማመዳችሁ በሔዳችሁ ቁጥር የኑሮ አጋራችሁን ልብ በማሸነፍ የበለጠ አዎንታዊ እንዲሆንና በመካከላችሁም ውጥረት ከማስፈን ይልቅ ፍቅር እንዲዳብር መሣሪያዎች ትሆናላችሁ፡፡
ባብዛኛው ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው ሊለዋወጧቸው የሚገቡ ገንቢ ቃላትን ችላ ይሏቸዋል፡፡ በየዕለቱ እርስ በእርስ በግልጽ እና በእውነተኛ ስሜት ላይ የተመሠረቱ የፍቅር ቃላትን መለዋወጥ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም በተጠራንበት የተቀደሰ የጋብቻ ጥሪ ምስክርነታችንን በታማኝነት እንድንወጣ ይርዳን፡፡




Comments