ውሃ ውይንስ የወይን ጠጅ?
- May 25, 2015
- 8 min read
Updated: Jan 11
አንድ ወዳጄ ነው፡፡ አንድ ቀን ወትሮ እንደምናደርገው በእርሱ መኪና የሆነ ሥራ ለማስፈጸም እየተጓዝን ሳለ በትዳሩ ውስጥ የገጠመውን ችግር አጫወተኝ፡፡ የውልሀ ሀብታሙ ሁለታችንም አግብተናል፡፡ ሁለታችንም ደግሞ ያገባነው ሴቶችን ነው፡፡ አንተ ደግሞ በትንሹ ለሰባት ዓመታት ያህል ትዳርን ከእኔ ቀድመህ ታውቀዋለህ፡፡ እስኪ ንገረኝ ትዳር ከመመሥረትህ በፊት የነበሩህ እነዛ ሞቃት የፍቅር ስሜቶች ይቀዘቅዛሉ እንዴ? ማለቴ ይጠፋሉ፣ ወይ ይቀየራሉ? አለኝ፡፡ ምንም እነኳን ሁለታችንም በተለያዩ ጊዜያት የየቤታችንን ችግሮች የምናወራ እና የመፍትሔ ሃሳብም በጋራ የምንፈልግ ቢሆንም የዛሬው ጥያቄው ግን አስደንግጦኛል፡፡ እናም “ምን አልከኝ?” አልኩት፡፡ በትዳሬ ላይ ያለኝ የፍቅር ስሜት ጭራሽ ቀዝቅዟል፡፡ አሁን ላይ ባለቤቴን ምንም አላፈቅራትም፡፡ ለስሜቷም ግድ የለኝም፡፡ ብታዝን፣ ብትደሰት፣ ብትወጣ፣ ብትገባ ምንም አይመስለኝም፡፡ በርሷም በኩል ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ነው የምገነዘበው፡፡ በቃ የትዳራችን ወዝ ተሟጧል፡፡ አልቆብናል፡፡ ስሜቱ በጣም እየጋለ ሄደ፡፡ አብረን መኖር የመቀጠላችን ትርጉሙም ግቡም አይገባኝም፡፡ አለኝ፡፡ እንዴ ገና እኮ ጥቂት ዓመታትን ነው አብራችሁ የኖራችሁት ደግሞመ ወልዳችኋል እኮ ከአንድም ሁለት ልጆች አልኩት፡፡ ሁኔታው ፈጽሞ ያላሰብኩት ስለነበረ ድንገት የመጣልኝ መላ እንጂ ያዋጣ ይሁን አይሁን እንኳን ለማመዛዘን ጊዜ አልወሰድኩም፡፡ እናም ብዙ አልጠቀመኝም፡፡ እና ልጆች አሉን በሚል በዚህ በተቀዛቀዘ ሕይወት እስከመቼ እቀጥላለሁ፡፡ ልጆች ምን ይሆናሉ፡፡ እኔና እርሷ እኮ አልተጣላንም ስሜታችንን በግልጽ ተነጋግረን የወደፊት ሕይወታችን ምን መምሰል እንዳለበት መወሰን እንችላለን፡፡ ከዚያ ልጆቻችንን በጋራ እናሳድጋለን፡፡ በርግጥ ኑሯቸው የተደላደለ እና ጥሩ የሚባል መተዳደሪያ ያላቸው በመሆኑ በኑሮ ማናቸውም እንደማይጎዱ አውቃለሁ፡፡ ሌላ ….. ብዬ ገና ሳልጨርስ ከአፌ ነጥቆ ጓደኛዬ ሙት በፈለከው ነገር እምልልሀለሁ በዚህ እነኳን አትጠርጥረኝ ከሷ ሌላ በሕይወቴ የገባች ማንም ሌላ ሴት የለችም፡፡ ችግሬ የነገርኩህ ነገር ብቻ ነው አለኝ፡፡
የማደርገው ነገር ግራ ግብት አለኝ፡፡ እኔ የሰባት ዓመት የትዳር ታላቁ ለዚህ ፈተና ላይ ለወደቀ ጓደኛዬ ምን ዓይነት ምክር ልለግሰው እችላለሁ፡፡ ምንስ አውቀት አለኝ፡፡ ብቻ ዝም ብዬ እንደመጣልኝ እስኪ እንጸልይበት አልኩት፡፡ ማታ ስገባ ለባለቤቴ ሁኔታውን አጫወትኳት፡፡ ባለቤቴ ደነገጠች፡፡ የዛን ዕለት ማታ ጉዳዩ በጣም አሳሰበን እና ጸለይንበት፡፡ የወዳጆቻችንን ቤተሰብ እግዚአብሔር እንዲታደገው ተንበርክከን ለረጅም ሰዓት ጸለይን፡፡
ግን ግን እውነት ፍቅር ይቀዘቅዛል? የትዳር ጣዕሙ ሙጭጭ ብሎ እንዲያልቅ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲህ ዓይነት ነገር በተከሰተ ጊዜስ ባለትዳሮች ማድረግ ያለባቸው ነገር ምንድነው? የሚኖረው ብቸኛ አማራጭ ፍቺ ነውን? ወይንስ ትዳር ይታደሳል? የነበረውን ጣዕምስ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበት ተእምር አለ? እስኪ መጀመሪያ ፍቺን በጥቂቱ እንመልከት?
በፍቺ የሚጎዳው ማን ነው? በዳይ ወይስ ተበዳይ?
በጋብቻ ውስጥ ግጭት በሚፈጠርባቸው ጊዜያት ሁለቱም ወገን አንዱን በዳይ በማድረግ ራሳቸውን እንደተበዳይ ይቆጥራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የበደሉ መጠን ለመሸከም ከሚቻለው በላይ መሆኑን በመግለጽ መፍትሔው መለያየት ብቻ እንደሆነ እምነት ያሳድራሉ፡፡ ለመሆኑ በመለያየት የሚጎዳው ማን ነው? በዳይ ወይስ ተበዳይ? ለመሆኑ እንደው በትዳር ውስጥ ከመጠን በላይ ተበድያለሁ የሚል ወገን ቢኖር እንኳን ከመለያየት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል?
እስኪ በአንድ ወቅት ካነበብኩት መጽሐፍ ያገኘሁትን ምሳሌ ላካፍላችሁ፡፡ ሁለት ወረቀቶችን ውሰዱና በሙጫ ሙሉ ለሙሉ አጣብቋቸው፡፡ ከደረቁ በኋላ ወረቀቶቹን ለማለያየት ብትሞክሩ ምን ይፈጠራል? ይበጣጠሳሉ፡፡ የትኛው ነው የበለጠ የሚበጣጠሰው? በትዳር ውስጥም መለያየት በሚፈጠር ጊዜ እንዲሁ ነው፡፡ የበደለውም ሆነ የተበደለው ሁለቱም ተጎጂዎች ናቸው፡፡ ማንም ከመለያየቱ ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ መለያየትም የበደል ካሳ ወይም የእረፍት እና የእፎይታ ጊዜ አይሆንም፡፡ ይልቁንም እንደወረቀቶቹ ጠዋት ማታ በጸጸት እስከመበጣጠስ የሚያደርስ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ትፈልጋላችሁ? በቅርብ የምታውቋቸው በፍቺ የተለያዩ ሰዎችን ጠይቋቸው፡፡ በእርግጥ የቅርብ ሰዋቸው ከሆናችሁ እና እውነቱን ከነገሯችሁ ከፍቺ የሚገኝ ምንም ጥቅም እንደሌለ በትክክል ትረዳላችሁ፡፡
መለያየት የሚያስከፍለን ዋጋ ትዳራችንን ለማቆየት ከምንጠየቀው መሥዋዕትነት እጅግ የበረታ ነው፡፡ ትዳራችንን ለመገንባት የሚጠበቅብን ሁለት ነገሮችን ብቻ ማከናወን ነው፡፡ መጀመሪያ ከክብር ዙፋናችን ወረድ ብለን በትኅትና ዝቅ ማለት፡፡ ከዚያ በኋላ ስሜታችን ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር የሚለንን ነገር ለማዳመጥ እና ለመፈጸም ራሳችንን አሳልፈን መስጠት፡፡ በቃ ከዚያ ሁኔታውን መለወጥ የእኛ ኃላፊነት አይደለም፡፡ በደንብ እንድትረዱኝ እፈልጋለሁ፡፡ የእኛ ኃላፊነት ወይን ጠጁ እንዳለቀብን አምኖ መቀበል እና ትዳራችንን ለማፍረስ ሳይሆን ለመጠገን መሻት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እግዚያብሔር የሚያዘንን ለመፈጸም መዘጋጀት፡፡ በቃ፡፡ ተአምራቱን ማከናወን የእኛ አይደለም፡፡
የትዳር ጣዕሙ ሙጭጭ ብሎ እንዲያልቅ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
ትዳር ሁለት በብዙ የማይተዋወቁ ሰዎች ሕይወታቸውን በጋራ ለመምራት የሚጣመሩበት ኩነት ነው፡፡ ሁለቱ በአመለካከት፣ በአስተዳደግ፣ በስሜት ደረጃዎች እና በመሳሰሉ መሠረታዊ ማንነቶች የየራሳቸው ማንነት ያላቸው ናቸው እንጂ ፍጹም አንድ አይደሉም፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ማንነታቸውን ይዘው ነው የሚጣመሩት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሁለቱም ወደኋላ ትተዋቸው የመጧቸው የሕይወት አቅጣጫዎች አሏቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የትዳር የመጀመሪያ ዘመናት እጅግ ፈታኝ ዘመናት ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ያወያየኋቸው በትዳር ከሃምሳ ዓመታት የበለጠ ጊዜ ያሳለፉ እና በቤተክርስቲያናችን ለአብነት የሚጠቀሱ ባለትዳሮች እንደዚህ ብለውኝ ነበር፡፡ የትዳር የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት እንደ ኮሮኮንች መንገድ ናቸው፡፡ ይጎረብጣሉ፡፡ ነበር ያሉኝ፡፡ የዚህ ደግሞ ምክንያቱ ባለትዳሮቹ ትተዋቸው የሚመጧቸው የሕይወት ልማዶች ነጸብራቅ አንዱ ነው፡፡ በአባትና በእናታቸው ቤት የነበራቸው የሕይወት ነጸብራቅ፣ ናፍቆቱ ገና ሙሉ በሙሉ ከሕይወታቸው የሚወጣበት ጊዜ አይደለም፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር በራሳቸው ውሳኔ እንደፈለጉ ይወስኑ የነበረበት ሕይወት በትዳር ውስጥ በተመሳሳይ ሊቀጥል ፈጽሞ አይችልም፡፡ የበለጠ ለቤተሰባዊ ሕግጋት የመታዘዝ ኃላፊነት ይገጥማቸዋል፡፡ ይህም እስኪለመድ እና እስኪዋሃደን ያስቸግረናል፡፡
ሌላው ዛሬ የትዳር ጓደኛችን ሳንጋባ በፊት ተቀጣጥረን በምንገናኝበት ጊዜ ተጣጥባ/ቦ፣ ተጨንቃ/ቆ ነበር ወደ እኛ የምትመጣው/የሚመጣው፡፡ ታጥበን፣ ተቀብተን፣ መስታወት ፊት ተመላልሰን፣ ይህም አልበቃ ብሎን ባካባቢያችን የለ ሰውን እንደሚያምርብን አረጋግጠን፣ ያለቀለት፣ ውብ እና ቆንጆ ሆነን ነው የምንገናኘው፡፡ ዛሬ በአንድ ቤት ስንኖር ግን እንደወረድን ነው የምንገናኘው፡፡ ቤት በምናዘወትርበት ብዙም ጥንቃቄ እና ትኩረት ባልተደረገበት ሁኔታ፡፡ በባህሪ ደረጃም ቢሆን ተገናኝተን የምንለያይ ባለመሆኑ በዚህ መታገስ እና ማሳለፍ አይስተዋልብንም፡፡ ሌላ ሕይወት ስለሌለን ሁሉ ነገራችን የሚገለጽበት መድረክ ይኸው ቤታችን ነው፡፡ ይህም እስኪለመድ እና በደንብ እስከምንተዋወቅ ይጎረብጠናል፡፡
ሌላው በበርካታ ቤተሰቦች የሚስተዋለው ልጆች በሚወለዱበት ጊዜ የሚፈጠረው የትኩረት አቅጣጫ መቀየር ነው፡፡ ትኩረታችን ወደ ልጆቻችን በሚገለበጥ ጊዜ የሚፈጠረው የስሜት መረበሽ ለቤተሰብ ሕይወት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ይገለጻል፡፡ ለልጆች ተገቢውን ትኩረት መስጠቱ ጤናማ ቢሆንም ነገር ግን የቤተሰቡ አባላት ሁሉ በየደረጃቸው ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለባቸው፡፡ በተለይ ባል እና ሚስቱ ለራሳቸው ለብቻቸው የሚሰጡት ጊዜ ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ እንደሚመቻቸው ዕቅድ በማውጣት አብረው ከቤት ውጪ በእግራቸው በመጓዝ መወያየት፣ ራት መገባበዝ፣ ለብቻቸው ልጆቻቸው በሌሉበት ሃሳባቸውን የሚለዋወጡባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
የገንዘብ አጠቃቀም እና ግልጽነት የሌለው የቤተሰብ ኢኮኖሚ አስተዳደር ሌላው መሠረታዊ የቤተሰብ ተግዳሮት ነው፡፡ የቤተሰቡን ገቢ እና ወጪ በግልጽ ማወቁ እና በቤተሰቡ ገቢ ላይ በጋራ የመወሰን ባሕልን ማዳበሩ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በመመካከር እና በጋራ በማቀድ አቅምን ያገናዘበ የአኗኗር ዘይቤን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ሁል ጊዜ ሳይታሰቡ ሊከሰቱ ለሚችሉ ሁኔታዎች ተቀማጭ ገንዘብ የመቆጠብን ባሕል ማዳበር አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ የአቆጣጠብ ዘይቤም ጤናማ አካሄድ አይደለም፡፡ በቤተሰባችን ውስጥ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ለማሟላት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡
ጾታዊ ግንኙነት ለበርካታ ቤተሰቦች ፈተና የሆነ ነጥብ ነው፡፡ ጾታዊ ግንኙነት በራሱ ጥበብ ነው፡፡ ሁለቱም ባልና ሚስቶች ስሜታቸውን በጋራ ማርካት እንዲችሉ በግልጽ መወያየት እና በራስ ደስታ ላይ ብቻ ሳያተኩሩ አንዱ ሌላውን ለማስደሰት ማድረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ መማር ካለበት መማር፣ ሌሎችን ማማከር ካስፈለገ ምክር መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ጥበብ እንደመሆኑ መጠን በግልጽ በመመካከር እና ከሌሎችም ልምድ በመውሰድ ልንካነው የምንችለው ነገር ነው፡፡ የሚያስፈልገው ዋና ነገር መተሳሰብ እና የሌላውን ደስታ ለማምጣት ከፍተኛ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ብቻ ነው፡፡
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ውስጥ በመሠረታዊነት ልንገነዘበው የሚገባው የሴቶችን እና የወንዶችን ተፈጥሯዊ የስሜት ሁኔታ መገንዘብ እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ በተፈጥሮ መሠረታዊ ልዩነቶች ያሏቸው በመሆኑ በዚያ ላይ ተገቢውን ግንዛቤ በማግኘት ለማሟላት መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ የራሱ የሆነ እውቀት እና ክህሎት ያሚያስፈልገው ነጥብ በመሆኑ ለመማር ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ የሴቶችን ወይንም የወንዶችን የተፈጥሮ የስሜት ሁኔታዎች ልታስተምረን/ሊያስተምረን የምትችለው/የሚችለው ሚስታችን/ባላችን እንጂ በመሥሪያ ቤት፣ በዝምድና ወይንም በጉርብትና የምናውቃቸው የቅርብ ሰዎቻችን እንዳልሆኑ ልብ ልንል ይገባል፡፡ በመሆኑም እኛ በግልጽ ተነጋግረን ካላዳበርነው ከውጭ በምናገኘው ምክር ብቻ ምንም ልናመጣ እንደማንችል ጠንቅቀን ማወቅ አለብን፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች በተጨማሪ በትዳር ውስጥ የፍቅር ተግዳሮቶች ከሆኑት ሁኔታዎች የሚከተሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
በፍቅር ግንኙነት ላይ ትንታኔ የሚሰጡ የስነልቦና እና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች በሰዎች መካከል የሚመሠረቱ የፍቅር ግንኙነቶችን በሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡ አንደኛው በአምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቻችን በሚደርሱን መረጃዎች ላይ ተመሥርተን የምንማረክባቸው የፍቅር ግንኙነት ዓይነት ሲሆን በእጅ በመንካት፣ በመሳሳም፣ ልብ በሚያቀልጥ የፍቅር ዕይታ በመተያየት፣ ቁሳዊ ስጦታዎችን በመለዋወጥ፣ በሻማ መብራት እና በሙዚቃ የታጀቡ የምሽት ግብዣዎችን በመገባበዝ የሚገለጽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ወደ ሁለተኛው እና ሦስተኛው ደረጃ መሸጋገር ካልቻለ ግን አላቂ ፍቅር ነው፡፡ ሙጥጥ ብሎ ያልቃል፡፡ አብዛኞቹ ትዳሮች በዚህ ደረጃ ላይ በሚገኙ እና ገና ወደ ሁለተኛውና ወደ ሦስተኛው ደረጃ ለማደግ ዕድል ባላገኙ የፍቅር ግንኙነቶች ላይ የሚመሠረቱ በመሆኑ በትዳር ውስጥ የፍቅር ስሜታቸው ሙጥጥ ብሎ ያልቃል፡፡ እንደድሮው በፍቅር መተያየት፣ በሻማ መብራት እና በሙዚቃ የታጀቡ ግብዣዎችን መገባበዝ በነበረው መልኩ ሊቀጥል አይችልም፡፡ በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን የሚደርሱንን መረጃዎች መሠረት በማድረግ የሚገነባ በመሆኑ በምናየው በምንሰማው እና በምንዳስሰው ነገር ላይ ለውጥ በተከሰተ ጊዜ ፍቅሩ የተመሠረተበት ነገር የተለወጠ በመሆኑ ፍቅሩም ይጠፋል፡፡
ሁለተኛው በአንደኛው ላይ ያየናቸው ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ከአንደኛው ግን ፈቀቅ ያለ ነው፡፡ ዘወትር አብሮ በመሆን እና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የአንዱ መራቅ ለሌላው ያጎድልበታል፡፡ ለሁለቱም አብረው መሆናቸው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ልክ አብዛኞቻችን በጋብቻችን የመጀመሪያ ወራት ላይ እንደምናደርገው፡፡ አብሮ ገበያ መሄድ፣ አብሮ የምሽት የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ገበታን ተጠባብቆ መመገብ፣ የተመገብንበትንባቸውን እቃዎች በጋራ ማነሳሳት፣ ማጠብ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አንዱ ለሌላው ያስባል፣ በተወሰነ ደረጃም መከባበር እና ቅድሚያ ለሌላው መስጠት ይስተዋልበታል፡፡ ይህም ግን ሊቀዘቅዝ እና መልኩን ሊቀይር የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉት፡፡ ሆኖም ግን በመጀመሪያ ደረጃ ከተመለከትነው የፍቅር ደረጃ አንድ እርከን ከፍ ያለ እና ጠቃሚ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ወደሦስተኛው ደረጃ እንዲያድግ እስካልተደረገ ድረስ ለዘላቂነቱ ዋስትና የለውም፡፡
ሦስተኛውን እና ለትዳር ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የፍቅር ደረጃ ከመመልከታችን አስቀድምን እስኪ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ነጥቦች እንመልከት፡፡
የትዳራቸው የፍቅር ስሜት የተቀዛቀዘ ሆኖ የሚሰማቸው ባለትዳሮች ማድረግ ያለባቸው ነገር ምንድነው?
የቃና ዘገሊላ ሰርግ
በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 2 ላይ የሰፈረውን የቃና ዘገሊላ ሰርግ ተአምራት በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ክስተቱ የተፈጸመው በሰርግ ግብዣ ላይ ነበር፡፡ በሰርጉ ግብዛ ላይ የሚፈለገው ነገር የወይን ጠጅ ነው፡፡ የወይን ጠጅ ጣፋጭ መጠጥ ነው፡፡ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የተነገረው ቁም ነገር አንድ እና አንድ ነው፡፡ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ፡፡” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልገጋዮቹን ጋኖቹን ውሃ እንዲሞሏቸው ጠየቃቸው፡፡ ውሃ ምንድ ነው? እጅግ ጠቀሚ ነገር ነው፡፡ ግን ጣዕም፣ ቀለም፣ ሽታ የለውም፡፡ እንዳውም የሆነ ነገር እንደማይጣፍጥ ለመግለጽ ውሃ ውሃ ይላል እንላለን፡፡ ከላይ ታሪኩን ያጫወትኳችሁ ጓደኛዬም ቃል በቃል “ትዳሬ ውሃ ውሃ አለኝ” ነበር ያለኝ፡፡ ይህንን ውሃ ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ወይን የቀየረው፡፡ ወይን ጣፋጭ ነው፤ አስደሳች ቀለም ማራኪ መዐዛም አለው፡፡
ኢየሱስም “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፡፡ ኢየሱስ ባዶውን ጋን ወይን መሙላት አይችልም ነበርን? አያችሁ ለኢየሱስ ተአምራትን እንዲያደርግ ዋናው ግብዓት የእናንተ አስተዋጽዖ እና ፈቃደኝነት ነው፡፡ ውሃችሁን በጋኖቹ ውስጥ በመሙላት በኢየሱስ ፊት ማቅረብ ከእናንተ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሰማችሁ ያለውን የመበደል፣ የባዶነት፣ ጣዕም የማጣት ወይም ሌላ ስሜት ወደጎን አድርጉት፡፡ ዋናው ነገር እናንተ አሁን እየተሰማችሁ ያለው ስሜት አይደለም፡፡ ለኢየሱስ አስፈላጊው ነገር መሻታችሁ ነው፡፡ መሻታችሁ ደግሞ በእዚአብሔር እና በቅዱስ ጉባኤው ፊት የገባችሁትን ቃል ኪዳን ማጽናት ነው፡፡ እስኪ አስቡት በቃና ዘ ገሊላ የነበሩትን የሰርግ ግብዣ አስተናጋጆች ከውርደት ለመታደግ ግድ የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ የአባቱን ትእዛዝ ላለማፍረስ ትግል በማድረግ መሥዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙትን ሰዎች እንዴት አይረዳችሁም፡፡
ትዳር የሚመራው በግብርና ህግ ነው፡፡ “የዘራኸውን …” በሚለው የሀገራችን ዕውቅ ብሂል፡፡ ትዳራችሁ ከደረሰበት ውድቀት እንዲያገግም ትፈልጋላችሁ? መጀመሪያ መልካም ዘርን ዝሩ ከዚያ የዘራችሁትን ዘር ተንከባከቡት ከዚያ ደግሞ እንክብካቤያችሁን ላፍታ እንኳን ሳታቋርጡ አድጎ ለምርት መሰብሰቢያ ዕድሜው እስኪደርስ ጊዜ ስጡት፡፡ የግብርና ሕግ ማለት ይሄ ነው፡፡ መዝራት፣ መንከባከብ እና በቂ ጊዜ መስጠት፡፡
ይህንን ራሳችሁ አድርጉት እንጂ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲያደርገው አትጠብቁ፡፡ መልካም ዘር ምንድን ነው፡፡ ራስን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር እና ለትዳር ጓደኛችሁ መስጠት፣ ይቅርታ ማድረግ እና ትኅትናን ማሳየት ናቸው፡፡ ከእኔነት ቀጠና መውጣት እና ራሳችንን ከሰቀልንበት የክብር ዙፋን መውረድ፡፡ እንክብካቤ ደግሞ የተዘራው ዘር ለማደግ የሚያስፈልገው ውሃ እና ምግብ ነው፡፡ እነርሱም ጸሎት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ ምሪቱን ማዳመጥ፣ ፍቅርን ለትዳር ጓደኛ መስጠት እና እንክብካቤ ማድረግ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በይደር ያቆየነውን ሦስተኛው እና ለትዳር እጅግ አስፈላጊ የሆነው የፍቅር ደረጃ እንመልከት፡፡ ይህ የፍቅር ሁሉ ጣራ እና መጽሐፍ ቅዱስ “ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ብሎ የመሰከረለት ነው፡፡ የነፍስ እና የስጋ ውኅደት ነው፡ ምንም ሳያስቀሩ ራስን ሙሉ በሙሉ መስጠት ነው፡፡ በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ከተመለከትናቸው የፍቅር ደረጃዎች ጋር በጥምረት ይሠራል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ፍቅር መለኮታዊ ነው፡፡ መሠረቱ ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ከላይ ይሰጣል እንጂ የስነልቦና መጣጥፎችን በማንበብ፣ በሥልጠና ወይም በአማካሪዎች ብልሃት አይገኝም፡፡ በጸሎት እና ራስን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፎ በመስጠት የሚገኝ ነው፡፡ በምንም ላይ አይመሠረትም፡፡ የሚወደውን ሰው የሚወድበትን ምክንያት እራሱ ይፈጥራል እንጂ በሚያየው፣ በሚሰማው እና በሚዳስሰው ነገር ላይ አይመሠረትም፡፡ ምላሹ ጥላቻ እንኳን ቢሆን እርሱ ግን መውደዱን አያቆምም፡፡ በደልን አይቆጥርም፣ አይታበይም፣ ይታገሳል፣ ቸርነትን ያደርጋል … 1ቆሮ. 13፡፡ እርሱም እግዚአብሔር የሰው ልጅን የወደደበት ወሰን የሌለው ፍቅር ነው፡፡ አያልቅም፣ አይደበዝዝም፡፡ በትዳር ውስጥ ያለው ፍቅር ወደዚህ በምንም ላይ ወደማይመሠረት የፍቅር ደረጃ በሚያድግበት ጊዜ የዘላቂነት ዋስትናውን ያገኛል፡፡ ያኔ የማያልቅ ጣዕም፣ የማይደበዝዝ ቀለም እና የማይቀየር መዐዛ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የትዳር ጣዕም ከተመሠረተበት ሁኔታ እና ከሚገኝበት የፍቅር ደረጃ ጋር በእጅጉ ይያያዛል፡፡ በሚያልቅ እና በሚደበዝዝ መሠረት ላይ በተጣለ ጊዜ ሁለት ክረምት እንኳን ሳይዘልቅ ውሃ ውሃ ሊል ይችላል፡፡
የትዳራችሁ ጣዕም ተጠብቆ እንዲቆይ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በሉ
በትዳራችሁ ውስጥ ራስ እና ሶስተኛ አካል ለሆነው ለእግዚአብሔር ተገቢውን ሥፍራ ስጡት
በየዕለቱ በጋራ ጸሎትን በማድረግ እና የእግዚአብሔርን ቃል በመከፋፈል የምትተጉ ሁኑ
በየጊዜው በመናዘዝ ቅዱስ ቁርባንን ተቀበሉ
ትዳራችን አብቅቶለታል ማንም አያነሳውም የሚለውን አስተሳሰብ አስወግዱ ኢየሱስ ይጠግነዋል
ወደፊት በትዳር ሕይወታችሁ የሚገጥማችሁን በትእግስት ለመወጣት ወስኑ
ባሳለፋችሁት ሕይወት የተፈጠሩ በደሎችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ተባባሉ
በጋብቻችሁ ውስጥ እንዲደረግለት የሚጠብቅ ሰው አትሁኑ ሁል ጊዜ የመጀመሪያውን እርምጃ የምትወስዱ፣ ሰጪዎች፣ ቀድማችሁ ምኅረት አድራጊዎች እና ይቅርታ ጠያቂዎች ሁኑ
ለሚፈጠርብን ስሜቶች ሌላውን ሳንወነጅል ስሜታችንን የመግለጽ ልምድን እናዳብር ለምሳሌ “አንተ ነህ ያበሳጨኸኝ” ከማለት ይልቅ “በተፈጠረው ነገር ተበሳጭቻለሁ” ማለት ትክክለኛው የስሜት አገላለጽ ነው “አረፈድክብኝ” ከማለት ይልቅ “ብዙ ጠበኩህ” ማለት ሌላውን ወገን ሳይወነጅሉ ስሜትን የመግለጫ መንገድ ነው
በትዳራችሁ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን በግልጽ እና በየተወሰነው ጊዜ የምትወያዩበትን ልምድ አዳብሩ
ለውጥ የጊዜ ውጤት ነው ስለዚህ አትታክቱ ጠብቁ! ጠብቁ! ጠብቁ! ሁል ለለውጥ በቂ ጊዜ ስጡት ስትጠብቁ ታዲያ ማድረግ ያለባችሁን ከማድረግ ሳታቋርጡ ነው እነጂ በመሰልቸት እና በመታከት ተሸንፋችሁ መሆን የለበትም





Comments