“እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ማንም አይለየው”
- May 1, 2013
- 2 min read
Updated: Jan 11
ትዳር በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ
ትዳር ራስን ለመተካትና አዲስ ሕይወትን ለመፍጠር ከእግዚአብሔር ጋር ትበብር የምናደርግበት በዚህች ዓለም የሚከናወን የወንድና የሴት የሠመረ የፍቅር ጥምረት ነው፡፡ አዲስ ሕይወትን የመፍጠር ሂደቱ ምሉዕ የሚሆነው ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ ፍጹም ትብብር በመሆኑ መንፈሳዊ ባኅሪም አለው፡፡ ትዳር በወንድና በሴት መካከል እስከ ሞት ጸንቶ እነዲቆይ የሚመሠረት የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡ ጥምረቱ የሚሰፋበት ሰበዝ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፡፡
በትዳር ውስጥ የእግዚአብሔር ሚና ባለትዳሮቹን በማገናኘት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሁለቱን በፍቅር የሚያስተሳስር ማሰሪያ ሆኖ ለዘላለም አብሯቸው የሚኖር ነው፡፡ በእርሱ እነርሱ ይተሳሰራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በምድር የሚገኝ ማንኛውም ኃይል፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴና የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት እንኳን ቢሆኑ የትዳርን ጥምረት ለመለየት አይችሉም፡፡ ማንም ሥልጣንም መብትም የለውም፡፡ ለዚህ ነው ካቶሊካውያን “እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ማንም አይለየው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሕሮ በልዩ አትኩሮት የሚገነዘቡት፡፡ ካቶሊካውያን ባለትዳሮች በምሥጢረ ተክሊል አማካኝነት በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ባለው መለኮታዊ አንድነትና ውጤታማ ፍቅር ይሳተፋሉ፤ በትዳር ሕይወታቸውም ቅድስናን ለማግኘት እርስ በእርሳቸው በመተጋገዝ ይህንኑ አንድነት ይመሰክራሉ፡፡ በተክሊል ምሥጢር ውስጥ በመኖራቸው በምዕመናን መካከል የተለየ ፀጋና ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ጸጋዎች በቤተሰባዊ ፍቅር በማሳደግ ሌሎችን በኑሯቸው ያስተምራሉ፡፡ ከተክሊል ትስስር ቤተሰብ ይወጣል፡፡ የዚህ አዲስ ቤተሰብ አባላት በጥምቀት አማካኝነት በሚቀበሉት የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፡፡ በዚህም ሕዝበ እግዚአብሔር ለብዙ ዘመናት እንዲኖሩና ቀጣይነት ባለው መልኩ እርሱን እንዲያከብሩ ያደርጋሉ፡፡ በማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ቢጓዙም እንኳን እግዚአብሔር አብ ፍፁም እንደሆነ ሁሉ በተለያዩ የኅንነት መንገዶች በመጠናከር የተክሊል ቃልኪዳናቸውን ጠብቀው ወደዚያ ፍጹም ቅድስና እንዲደርሱ በእግዚአብሔር ተጠርቷዋል፡፡ ካቶሊካውያን ባለትዳሮች በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ በተለይ ለልጆቻቸው የመጀመሪያዎቹ የእምነት ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንንም በቃልና በአብነት ሊወጡት የሚገባ ተልዕኮ ነው፡፡ ትዳር ራሱን የቻለ ተቋም ነው፡፡ ጽኑ ሆኖ ይቆይ ዘንድ በውስጡ ለሚኖሩተረ ጥንዶች ምቹ የሆነና ልጆችን በመልካም ሥነ ምግባር ለማሳደግ በበቂ የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተምሕሮ መሠረት ትዳር ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖር የጠበቀ ግንኙነት የሚፈጠር ቤተሰባዊ ፍቅር ነው፡፡ በመሆኑም በእግዚአብሔርና በቅዱስ ጉባኤው ፊት በሚደረግ ቃልኪዳን በይፋ ይመሰረታል፡፡ ሁላችንም በዚህች ዓለም ስንኖር ወደ አባታችን ወደ እግዚአብሔር በሚደረግ የመልስ ጉዞ (ንግደት) ላይ ነን፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር የመኖራችን ምክንያትና የደኅንነታችን ምንጭ ነው፡፡ ወደዚህ ዓለም የመጣነው የወንድና የሴት የእርስ በእርስ ፍቅር እና ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖር ትብብር ፍሬዎች ሆነን ነው፡፡ በፍቅር መፈጠር፣ በፍቅር መወለድ፣ በፍቅር እና በእንክብካቤ ማደግ፣ ፍቅርን ያለማሰለስ ሕይወታችንን ሁሉ መፈለግ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ፍቅር ተነስተን ወደእግዚአብሔር ፍቅር በሚደረግ ጉዞ(ንግደት) ውስጥ መኖር የኛ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባኅሪ ነው፡፡ በዚህ የመልስ ጉዞ የሚኖሩ ሰዎች ሁለት ምርጫዎች አሏቸው፡፡ እነሱም በትዳር ወይም በንጽህና መኖር ናቸው፡፡ በትዳር የሚኖሩ ሕወታቸውንና ፍቅራቸውን በጋብቻ ውስጥ ከትዳር አጋራቸው እና ከልጆቻቸው ጋር በመጋራት ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆኑና በመልሱ ጉዞ አዳዲስ ሕይወትን በማፍራት ተሳታፊ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይገባል፡፡ በንጽህና ለመኖር የመረጡ ደግሞ በጋብቻ ከሚኖሩት ይልቅ ወደ ቅድስና ለመቅረብ ቀላሉን መንገድ መርጠዋል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ “ላላገቡና ለመበለቶች …እንደኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው…” ብሏልና 1ቆሮ 7፡8 ፡፡ ስለጋብቻ ስናወራ ሁለት ዓይነት ጋብቻዎች መኖራቸውን ልብ ማለት ይኖርብናል፡፡ አንደኛው ሰዎች ከክርስቶስና ከቤተክርስቲያኑ ጋር በድንግልና ለመኖር ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰዎች ከክርስቶስና ከአስተምሕሮዎቹ ጋር በመቆራኘት በትዳር ውስጥ ሃይማኖታዊ ሕይወትን ለመምራት የኑሮ አጋርን በመምረጥ የሚፈጽሙት ጋብቻ ነው፡፡ በሁለቱም ምርጫዎች በተግባርና በአብነት ወንጌልን በሕይወታችን እንድንመሰክር ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎብናል፡፡ በትዳር ለመኖር የመረጡ ወደእግዚአብሔር የሚያደርጉት የመልስ ጉዞ የተቃና ይሆንላቸው ዘንድ በጉዞው የሚያግዛቸውን የኑሮ አጋር ይመርጣሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር በምናደርገው የመልስ ጉዟችን አጋራችን እንዲሆን የምንመርጠው ምርጫ በሕይወታችን እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ በጥንቃቄ መከናወን አለበት፡፡ ካቶሊካውያን ትዳርን እንደከፍተኛ ኃላፊነት ሊቆጥሩት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጋብቻ ውስጥ የሚኖሩ ጥንዶች እያንዳንዳቸው ራሳቸውን በሙላት ለሌላው አጋራቸው እስከ ሞት ለመስጠት በሚገቡት ቃል ኪዳን ጸንተው እንዲኖሩ ይጠበቅባቸዋልና ነው፡፡ በዚህም የቤተሰቡ አንድነትና ፍቅር የበለጠ ይጠነክራል፡፡ የትዳራቸው ለዛና ጣዕም አስደሳች ይሆናል፡፡





Comments