የእግዚአብሔር ጸጋ
- Oct 13, 2024
- 3 min read
Updated: Jan 11

ለቅዱስ አንጦንዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነጋዲያን የቀረበ
ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.
ልደታ ማርያም (ካቴድራል) አዲስ አበባ
ከፍጥረት አንሥቶ የነበረውን የሰው ልጅ ታሪክ ስንመረምር አዳምና ሔዋን በመጀመሪያ እግዚአብሔር በሚመላለስበት በዚያ በእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ኀፍረት የሚባሉ ነገሮች አያውቋቸውም ነበር፡፡ ኋላ ላይ ሰው በወደቀ ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ ከላያቸው ላይ ተገፈፈ፡፡ መፍራት፣ መሸሽ፣ መደበቅ ሀብታቸው ሆነ፡፡ አዳምም ትላንት “ከሥጋዬ የተገኘች ሥጋ ከአጥንቴ የተገኘች አጥንት” ብሎ በደስታ ባዜመላት በሔዋን ፊት ዕርቃኑን ሊቆም አልተቻለውም፡፡ ኀፍረቱን ይሸፍንበት ዘንድ ቅጠል ሽምጠጣ ገባ፡፡ ሔዋንም እንዲሁ፡፡
እግዚአብሔር ግን የሰው ልጅን ይወደው ነበርና ከበግ ለምድ ልብስን ሰፍቶ አለበሰው፡፡ ከገነት ወጥቶ በምድር በሚኖርበት ጊዜ ሁሌ የተለያዩ እረኞችን እየላከ መራው፡፡ በሙሴ ጊዜም ሕግን ሰጠው፡፡ ሰው ከጸጋ በታች መሆኑ ቀርቶ ከሕግ በታች ሆነ፡፡ ያውም ሊፈጽመውና ሊጸድቅበት የማይችለው ጥብቅ ሕግ፡፡
ሰው ታሪኩ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ የእግዚአብሔር ዕቅድ አልነበረምና ቅዱስ ገብርኤል “ጸጋን የተሞላሽ ሆይ!” ብሎ ሰላምታ ያቀረበላት ቅድስት ድንግል ማርያም በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ተገኘች፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞም ለደኅንነት ዕቅዱ ማስፈጸሚያ አስቧት ነበርና ከአዳም ኃጢያት ከልሎ አዘጋጃት፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ የሰው ልጅ በሆነችው በማርያም በሙላት አደረ፡፡ በእርሷም አላበቃም በእርሷ በኩል ቃል በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ደግሞ አደረ፡፡ ዮሐ. 1፡14-16 ከዚህ በኋላ ከሕግ በታች መሆናችን አብቅቶ ዳግም ጸጋውን ታደልን፡፡ ዘለዓለማዊ ወደሆነው መለኮታዊ ሕይወት እንድንደርስ ሊያግዘን የእግዚአብሔር ጸጋ ወረደልን፡፡
ለመሆኑ ጸጋ ምንድን ነው
እግዚአብሔር ልጆቹ እንድንሆን ላቀረበልን ጥሪ ምላሽ መስጠት እንድንችል እና የመለኮታዊ እና የዘላለማዊ ሕይወት ተቋዳሽ እንድንሆን የሚረዳን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሮሜ. 6፡23
የጸጋ ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከእርሱም ጸጋውን ለሁላችንም እንደዝናብ ይዘንብልናል፡፡ ዝናብ ከሰው ሰው ለይቶ አይዘንብምና የእግዚአብሔር ጸጋም ለሁልችንም ይዘንብልናል፡፡ ነገር ግን ሁሉ በነጻ ከፈሰሰው የጸጋ ዝናብ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንደሚያስገነዝበን ጸጋ ለትኁታን ብቻ ትሰጣለች፡፡ 1ጴጥ. 5፡5 ጸጋ “እንደዚህ እንደባሪያ ስላላደረከኝ አመሰግንሃለሁ …” የሚል የትዕቢት ጸሎት ለሚያደርሱት ሳይሆን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንኳን ለማድረግ ድፍረት ለሌላቸው ተንበርክከው “በእኔ ክፋት፣ በእኔ ክፋት፣ በኔ ብዙ ክፋት…” እያሉ ደረታቸውን ለሚደቁት ለትኁታን ነው የምትሰጠው፡፡
የጸጋ ጠቀሜታ ምንድን ነው?
እግዚአብሔር የጠራን በምንኖርባት ዓለም የወንጌሉ ምስክሮች እንድንሆን በሃሳባችን፣ በቃላችን እና በተግባራችን ታማኝ ሕይወት እንድንመራ ነው፡፡ እኛ ግን በየዕለቶ 70 x 7 ጊዜ እንወድቃለን፡፡ በዙሪያችን የጦርነት፣ የጥቃት፣ የዕልቂት ወሬ፣ የአዕምሮ ጭንቀት፣ የኑሮ ትግል፣ ትዕቢት ሌሎችም በርካታ ተግዳሮቶች ታማኝነታችንን ይፈትኑታል፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ስንሄድ ምንም ያህል ታማኝ ለመሆን ብንሞክር ከመስመር እንድንወጣ እንገደዳለን፡፡ ተጎትተን ያለእምነት እና ፍላጎታችን ወደኃጢያት እንወሰዳለን፡፡ ታዲያ ረዳት አያስፈልገንም? እንዴታ? ያስፈልገናል እንጂ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ የሚረዳን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ጸጋ የምንለው፡፡
ጸጋ የሚገኘው ከምሥጢራት ነው፡፡ ምሥጢራትን መቀበል ብቻ ሳይሆን ማዘውተር ጸጋን ያድለናል፡፡ ገና ሕጻን ሆነን ሳለ በምሥጢረ ጥምቀት አማካኝነት ጸጋን እንቀበላለን፡፡ “ሕጻን ምን ያውቃል ለራሱ ክፉ እና ደጉን እንኳን ያልለየ የእግዚአብሔር በግ ነው” ትሉኝ ይሆናል፡፡ ከአባቱ ከአዳም ኃጢያት የተነሳ እርሱም ከእግዚአብሔር ክብር ጎድሏልና የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈልገዋል፡፡ በምስጢረ ጥምቀት ጸጋ ከታደሰ በኋላ ነው የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ በተቀበልናቸው እና በምናዘወትራቸው ምሥጢራቶች ሁሉ የእግዚአብሔር ጸጋ እንቀበላለን፡፡ በተናዘዝን ቁጥር ጸጋ በሕይወታችን ላይ ይጨመርልናል፡፡ ቅዱስ ቁርባንን ባዘወተርን ቁጥርም ጸጋው እጥፍ ድርብ ይሆንልናል፡፡
ወገኖቼ ሰው ሁሉ በሰውነቱ ለእግዚአብሔርን ጥሪ ምላሽ ሊሰጥ አይቻለውም፡፡ ምክንያቱም ያለምንም መለያ ሁሉም የእግዚአብሔር ክብር ጎድሏቸዋል፡፡ ነገር ግን ቤዛ ከሆነልን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጸጋው ለዘለዓለም ሕይወት እንበቃለን፡፡ ሮሜ. 3፡24 ከጸጋው የተነሳ መልካም ባል፣ መልካም ሚስት፣ መልካም ወላጅ እንሆናለን፡፡ መልካም ባልንጀራ፣ መልካም ካህን፣ ታታሪ ሠራተኛ፣ መልካም አስተዳዳሪም የምንሆነው ስለተማርን እና ስላነበብን ሳይሆን ቤዛ ከሆነልን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የተነሣ ነው፡፡
ቅዱሳን በዘመናቸው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ወንጌሉን በኑሯቸው በመመስከር የቅድስና ሕይወትን መምራት የቻሉ በመሆናቸው ሕይወታቸው ለእኛ እጅግ የበዛ ጸጋ ለሚያስፈልገን ለዚህ ዘመን ሰዎች አብነት ነው፡፡ የተጓዙበትን የሕይወት ጎዳና እንመርምር ምልጃቸውንም እንለምን፡፡ በመጀመሪያ ቁርባን ትምህርታችን ጊዜ እንደተማርነው ያለ ጸሎት ጸጋ ያለ ጸጋም ደኅንነት አይገኝምና በጸሎት እንበርታ፡፡ ከሁሉ የሚበልጠውን ጸሎት ሥርዓተ ቅዳሴን እናዘውትር፡፡ የእመቤታችንን የመቁጸሪያ ጸሎትን፣ የመለኮታዊ ምኅረት አክሊልን፣ የቅዱስ ልበኢየሱስን፣ የቅዱስ ፍራንቺስኮስን እና ሌሎችንም የቤተክርስቲያናችንን የጸሎት ሃብታት እንጠቀምባቸው፡፡ የጸጋ መወጣጫዎች ናቸውና፡፡




Comments