top of page

መሸፈኛ

  • Feb 15
  • 2 min read

ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ ነገሮች ሁሉ የተበላሹበት ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል። ሆኖም ኝ በዚያ ውድቀትና ሀፍረት ውስጥ አስቀድሞ የተገለጠው የምስራች (የወንጌል) ብርሃን ምሥጢር ይገኛል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ መጀመሪያ የተሰማቸው ስሜት ሀፍረት ነበር። ያደረጉትም ነገር የወደቀውን የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ምላሽ ነበር፤ ተሸሸጉ። የበለስ ቅጠሎችን ሰፉ። በራሳቸው ጥረት ሃፍረታቸውን ለመሸፈን ሞከሩ። ገና የእግዚአብሔርን ድምጽ እንኳን ከመስማታቸው በፊት፣ የሰው ልጅ ራሱን ከሃፍረቱ ለመሸፈን ጥረት መጀመሩን እንመለከታለን።

ቀጥሎ የሆነው ነገር ግን እጅግ አስገራሚ ነው። እግዚአብሔር የእነርሱን የበለስ ቅጠል አልተቀበለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፦ “እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፤ አለበሳቸውም” ይላል። ይህች አንዲት ዓረፍተ ነገር ሁሉንም ነገር ትለውጣለች። መሸፈኛውን ያዘጋጀው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ያ መሸፈኛ ደግሞ ደምን የሚጠይቅ መሸፈኛ ነበር። በደለኛ የሆኑ ሰዎች በሀፍረት ሳይዋጡ በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንዲችሉ፣ አንድ ንጹሕ የሆነ ፍጥረት ስለእነርሱ የደም ዋጋ መክፈል ነበረበት። ምክኛቱም ቁርበት እንዲሁ አይገኝም አስቀድሞ የጠቦቱ ደም መፍሰስ አለበትና ነው።

ይህ በተግባር የተገለጠ ሥነ-መለኮት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኃጢአት ምክንያት ደም ፈሰሰ። ደሙ የፈሰሰው በሰው ልጅ ላይ ቁጣን ለማፍሰስ ሳይሆን፣ ለሰው ልጅ ዝግጅትን ለማድረግ ነው። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን የገዛ ሃፍረታቸውን እንዲሸፍኑ አልተዋቸውም ውይንም  “ይበልጥ ትጉ”፣  “ለሚቀጥለው ጊዜ ተጠንቀቁ” አላላቸውም። ይልቁንም እርሱ ራሱ ሸፈናቸው።

ይህ እውነት ብዙ ጊዜ የምንስተውን ምስጢር ይገልጣል። ኃጢአት በራስ በጥረት አይወገድም፤ በመስዋዕት ይሸፈናል እንጂ። የበለስ ቅጠል የራስን ጥረት፣ አፈጻጸምና መሸሸግን ይወክላል። ቁርበት ግን የተሰጠ እንጂ የተገኘ አይደለም። እግዚአብሔር ሰው የሠራውን እርሱ ባዘጋጀው ተካው። ወንጌል የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። የሰው መፍትሔ በቂ አይደለም፣ ጠፊ፣ የማይዘልቅ ነው፤ የእግዚአብሔር መፍትሔ ግን ዋጋ የተከፈለበትና ዘላቂ መሸፈኛ ነው።

የድርጊቱን ቅደም ተከተል ልብ በሉ። እግዚአብሔር የሸፈናቸው ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ነው። ቸርነቱን ለማሳየት እስከ ስደት ድረስ አልጠበቀም። መከራና ቅጣት ስለሚመጣ ዝግጅቱን አላቋረጠም። ወደ ወደቀው ዓለም ሲወጡ እንኳ ተሸፍነው ነው የወጡት። ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ሃፍረት ተወገደ። እግዚአብሔር ማንነታቸው በራቁትነታቸው ወይም በውድቀታቸው ሳይሆን፣ እርሱ ባለበሳቸው ልብስ እንዲገለጽ አደረገ።

ይህ ቅጽበት ወደፊት ለሚመጣው ታላቅ ነገር ጥላ ነው። መሸፈኛ ሁልጊዜ የሚመጣው ከሰው ልጅ ውጭ እንጂ ከውስጡ አይደለም። ንጹሕ የሆነው አካል በበደለኛው ምትክ ይሞታል። ሰው ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እጅ እንጂ በገዛ እጁ አይሸፈንም። ሕግ ከመሰጠቱ፣ መቅደስ ከመገንባቱና መስቀሉ ከመቆሙ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ እግዚአብሔር ሰለሚፈጽመው ቤዛነት እየገለጠ ነበር።

ብዙ አማኞች ዛሬም የሚኖሩት በ“በለስ ቅጠል” እምነት ውስጥ ነው። ገጽታቸውን ብቻ ይገነባሉ፣ ድካማቸውን ይክዳሉ፣ በሥራ ጽድቅን ለማሳየት ይተጋሉ። ነገር ግን የበለስ ቅጠል ዘላቂ እንዲሆን አልታሰበም፤ ይደርቃል፣ ይረግፋል፣ ይወድቃል። እግዚአብሔር የሰው ልጅ የገዛ ሃፍረቱን የመሸፈን ከባድ ሸክም እንዲሸከም በፍጹም አልፈለገም።

የዚህ እውነት ተግባራዊ ምላሽ ራስን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ነው። መስፋቱን አቁሙ፤ መሸሸጉን ተዉ፤ የውሸት ማንነት መገንባቱን አቁሙ። እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ መሸፈኛ አስቀድሞ አዘጋጅቷል። በእግዚአብሔር ፊት የምትቆሙት ሃፍረታችሁ እየታየ በመሳቀቅ ሳይሆን፣ እርሱ ራሱ በሠራው ልብስ ተጎናጽፋችሁ ነው። ያ መሸፈኛ ከመስዋዕት የተገኘ ነው።

እግዚአብሔር በእውነት ከጎናችሁ የሆነው በኢየሱስና በመስቀሉ ምክንያት ነው። በኦሪት ዘፍጥረት በቁርበት የጀመረው ታሪክ በክርስቶስ ፍጻሜውን አግኝቷል። ኢየሱስ ሃፍረትን እንዴት እንደምንቋቋም ምክር ብቻ አልሰጠንም፤ እርሱ ራሱ መሸፈኛችን ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ አማኞች “ክርስቶስን ለብሰዋል” ይላል። ይህ ዝም ብሎ ለምቾት የሚነገር ምሳሌያዊ ንግግር ሳይሆን የቃል ኪዳን እውነት ነው። ሃፍረት ሁሉ  በእርሱ በመሸፈን ይወገዳል።

እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ማልበሱ አንድ መሠረታዊ ነገር ይነግረናል፦ እግዚአብሔር የተሰበሩ ሰዎች ወደ እርሱ ከመቅረባቸው በፊት ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ አይጠይቅም። እንዲቆሙ እንዲችሉ እርሱ ወደ እነርሱ ይመጣል፣ ይሸፍናቸዋልም። ወንጌል በቃል ትዕዛዝ አልጀመረም፤ በመሸፈኛ ጸጋ እንጂ።

መሸፈኛ ሁልጊዜም የሚገኘው ከመስዋዕት እንጂ ከራስ ጥረት አይደለም።


 
 
 

Comments


bottom of page