top of page

ጾም ምንድ ነው?

  • Jan 11
  • 3 min read

Updated: Feb 22

 


የነፍስ እና የሥጋ ኅብር የሆነው ሰው ስብዕናው አምስት ማንነቶችን ያዘለ ነው። ሰው የአካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ማንነቶች ጥምር ነው፡፡ ኣካላዊ ማንነታችን ውበት እና ገጽታችን ላይ እንድናተኩር የሚፈልገው ማንነታችን ነው፡ ስሜታዊ ማንታችን ደግሞ ደስታ፣ ፈንጠዚያ እና መዝናናትን ማዘውተር ትፈልጋለች። ስነልቦችን የሚያውቀውና የሚማረው ማንነታችን ሲሆን ባወቀ እና በተማረ ቁጥር ደግሞ ለዝና እና ለክብር ይሸነፋል፡ ማሕበራዊ ማንነታችን ደግሞ ከምንኖርበት አካባቢ ጋር የተቆራኘ፣ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ ወዳጅ፣ ከባልንጀራ እና ባጠቃላይ ከሰው፣ ከእንስሳ እና ከአካባያችን ጋር ያለንን ግንኙነት የምታካትት ናት። መንፈሳዊ ማንነታችን ግን ዘወትር እግዚአብሔርን የምትፈልግ ናት፡፡


እነዚህን የማንነታችንን ንዑሳን ክፍሎች ከተመለከትን ጾም ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ይሆንልናል። ጾም ማለት ውበት፣ ደስታ፣ ፈንጠዝያ፣ ክብር፣ ዝና ወዘተ ማንነቶቻችን “ለጊዜው ዝም በሉ እግዚአብሔርን አብዝታ ለምትፈልገው ለነፍሴ ዕድል ፈንታ ስጧት” የምንላቸው ጊዜ ነው። ትኩረታችንንም በመንፈሳዊ ማንነታችን እና በማሕበራዊ ግንኙነታችን ላይ በማድረግ ራሳችንን የምንረዳበት ወቅት ነው፡ በቀላል አገላለጽ እግዚአብሔርን እና ወገኖቻችንን የምናስብበት ወቅት ማለት ነው።

ይህንን ማድረግ ታዲያ እንደምናነበው ቀላል አይደለም ለምን ብትሉ ሥጋ ብርቱ ነው፡፡ በጠገበ እና በተመቸው ጊዜ ለነፍስ በቀላሉ ዕድል አይሰጣትም ሥጋ ደስ የሚያሰኘውን እየፈጸመ መኖርን ይሻል። ነፍስ እድል እንድታገኝ ሥጋችንን ማድከም ጠቃሚ ነው፡፡ ሥጋ ደግሞ የሚበረታው በበላ እና በጠጣ መጠን ነው፡፡ ስለዚህም ሥጋን በእጅጉ ከሚያበረቱ ምግቦች እና የተለያዩ የደስታና የፍስሃ ተግባራት በልዩ ሁኔታ መታቀብ አሥፈላጊ ነው፡ ሥጋ ሲደክም በነፍስ ውስጥ ያሻውን አያደርግም ነፍስም እጅግ ትበረታታለች። ስለእግዚአብሔር እና ስለወገኖቻችን እንድናስብ ትወተውተናለች፡ ከምግብ እና ከመጠጥ ብቻም ሳይሆን በጆሮ ከሚገቡ፣ በዓይንም ከሚታዩ ወይም ሌሎች አግባብነት ከሌላቸው ደስታን እና ፈንጠዚያን ከሚያቀርቡልን ሁኔታዎች እራሳችንን ማቀብ ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከእግዚአብሔር ጋር የምናሳልፍባቸውን ጊዜያት ከፍ በማድረግ፣ የሚያስደስቱን እና የምንወዳቸውን ነገሮች በመተው በጸሎት እና በሱባኤ የጾም ወራትን ብናሳልፍ በረከቱ እጥፍ ድርብ ይሆንልናል።


የጾም ዋና ተግባራት ጸሎት እና ልግስና ናቸው፡ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንደርሳለን፡ በግልና፣ በቤተሰብ እንዲሁም በቤተክርስቲያን በሚዘወተሩ ጸሎታት እንዲሁም በምሥጢረ ንስሃ ከወትሮው በላቀ ሁኔታ በመሳተፍ መንፈሳዊ ሕይወታችንን እናጠናክር። በልግስና ደግሞ ወደ ወንድምና እህቶቻችን እንደርሳለን። ልግስና ስንል ፍቅር፣ ጊዜ፣ ገንዘብ ወይም ደግሞ ራሳችንን ሊሆን ይችላል። በልግስና የምንጎበኛቸው ሰዎችም በጎዳና ጨርቅ አንጥፈው የተቀመጡትን ብቻ ሳይሆን በቤታችን፣ በሥራ ገበታችን፣ በመኖሪያ አካባቢያችን ወይም በቁምስናችን ያሉ በርካቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የምንችለውን ነገር ሁሉ እናድርግላቸው።


በጾም ወራት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት መታደስ አለበት፡ በእነዚህ የጾም ወራት እያንዳንዱ ክርስቲያን ዓለምን ጠፍሮ ካሰራት “ስለሌሎች አያገባኝም” ከሚል ስለራስ ብቻ በማሰብ ላይ ከሚያተኩሩ ዕኩይ አስተሳሰብ ዓለም እንድትላቀቅ እግዚአብሔር እንዲረዳን እንጸልይ።


የምናደርገውን ሁሉ ለታይታ እና ጠንካራ ክርስትያኖች መሆናችንን ለማስመስከር ከማድረግ እንድንቆጠብ፣ በግብዝነት ወጥመድ ተጠልፈን ከንቱ ውዳሴ፣ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ፡ ጌታ በበረሃ በቆየባቸው ወራት ያጋጠመውን ፈተና ማስተንተን የጾም ወራታችንን በድል እንድንወጣው ያግዘናል፡ ሰይጣን፣ በሀብት፣ በሥልጣን፣ በግብዝነት ሊፈትነው እንደፈለገ ሁሉ እኛም ዛሬ “ከአፍ የሚወጣ እንጂ ወደ አፍ የሚገባ አያስኮንንም” የሚሉ “ለምን ይህንን ድንጋይ ዳቦ አድርገህ አትበላውም” የሚለው ፈተና ግልባጭ ፈሊጦችን ጠንከርን መዋጋት ይጠበቅብናል።


አንዳንድ ጊዜ ማዘውተር የምንወደውን ነገር በመተው እና ለእርሱ የምናውለውን ገንዘብ በመቆጠብ ወይም ለወትሮ ከከምናከናውኗቸው ተግባራት ላይ ሰዓት በመቀነስ ለጸሎት ወይንም የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ በማዋል ጾማችንን የበለጠ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን። ቤተክርስቲያን ከምታዘን በተጨማሪ ልባችን የወደደውን በጎ ተግባራት ሁሉ ማድረግ እንችላለን። ከቤተክርስቲያን በተለያዩ ምክንያቶች ግልጽ ፈቃድን አግኝተን ካልሆንን በቀር ቤተክርስቲያን የምታዝነንን አጽዋማት በገዛ ፈቃዳችን በሌላ መተካት አንችልም ።


የሕይወታችን ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡ ጾም የትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ብንሆን እግዚአብሄርን ለማሰብ መልካም አጋጣሚ ነው፡ ሕጻን ብንሆን አዛውንት፣ ብርቱ ብንሆን ደካማ፣ በዚህ የጾም ወቅት እግዚአብሔርን ማሰብ መልካም ነው። እግዚአብሔር የጉብዝናችንን ወራት ጠይቆናል፡፡ ስለዚህ ወጣቶች በጾም ወራት በትጋት መሳተፍ አለባቸው ዕድሉን ለአዛውንት እና አረጋውያን ብቻ አሳልፈው መስጠት የለባቸውም። የወጣትነት ዕድሜ እግዚአብሔርን ለማሰብ እጅግ የተሰጠ መሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር እድሜአችንን ጠቅሶ "በጉብዝናህ" ብሎናል ስለዚህ ወጣቶች ሆይ በጸሎት እንበርታ። በደም ከአቤልም ከቃየልም ብንዛመድም መሥዋዕታችንስ የአቤል ይሁን፡፡ መጀመሪያችንን ከዚያም በኋላ የእድሜአችንን ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር እናድርግ። የጾም ወራትን በምናጠናቅቅበት ጊዜም ከመንፈሳዊ ሕይወት ጠቅልለን በመውጣት ወደ ዓለም የምንመለስበት ወቅት አይደለም። ይልቁንም በጾም ወራት ቤተኛ የሆንንበትን የመሥዋዕተ ቅዳሴ እና የንስሃ ምሥጢር የምናድስበት፣ በታደሰ እና በተለወጠ ማንነት ላይ በዚያው በቤታችን የምንቆይበት፣ በመንፈሳዊ ሕወታችን ዘንድሮ አንድ እርከን ለከርሞው ደግሞ ሌላ አንድ እርከን የምናድግበት ነው። እንጂ ጾም በመጣ እና በወጣ ቁጥር እየገባን እየወጣን እዚያው የምንመላለስበት ሕይወት አይደለም። የመንፈሳዊ ሕይወታችን ዕድገት የበላነው እና የተውነው የምግብ ዓይነትም አይደለም። በጸሎት ልምምድ፣ በንስሃ የምንልቅበት እንጂ። በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንታደስ ለወገኖቻችን አስተማሪ ሕይወት እንኑር።

 
 
 

Comments


bottom of page