ከእናንተ እያንዳንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም
- Oct 14, 2024
- 3 min read
Updated: Jan 11
በሀብታሙ አብርደው በጡረ
የ2007 ዓ.ም. የቅዱስ ገብርኤል ኖቬናን በማስመልከት የተዘጋጀ ታሕሣሥ 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

“ከእናንተ እያንዳዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም፡፡ እንዲሁም የኢየሱስን ሕግ ትፈጽማላችሁ፡፡” (ገላ. 6፡2)
ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፈላቸው ይህ መልዕክት ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም “የሌላውን ሸክም መሸከም” እና “የኢየሱስን ሕግ መፈጸም” ናቸው፡፡ ሸክም ምንድን ነው?
ሰዎች ስንባል በዚህ ዓለም በምንኖርበት ጊዜ ሁሉ ሁለት ዓይነት ሸክሞች አሉብን፡፡ አንደኛው ማንም ሊያግዘን የማይችልና እራሳችን ብቻ የምንወጣው ነው፡፡ ለምሳሌ ታታሪ ሠራተኛ መሆን፣ ታማኝ ባል ወይም ሚስት መሆን፣ መልካም ወላጅ መሆን እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ ሌሎች ሊያግዙን እኛም ሌሎችን ልናግዛቸው የምንችላቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ጳውሎስ “እንዳንዱ የሌላውን ሸክም ይሸከም” ባለበት በዚሁ የመልዕክቱ ክፍል “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ይሸከም” የሚለን፡፡ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሸክም በማለት የሚገልጸው ምንድን ነው? ለሰው ሸክሙ ምንድን ነው? እኔ ለበርካታ ጊዜያት ለሰው ሸክሙ የሚመስለኝ ማዘኑ፣ ማጣቱ፣ እና በኑሮው የሚገጥሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም ሰውን በቁሳዊ ጉድለቱ መደገፍ እና በርሕራሔ አብሮነታችንን ማሳየት ሸክማቸውን እንደማገዝ እቆጥረው ነበር፡፡ እንደዚህ ማሰቤ ምንም ጥፋት የለውም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ትምህርት ዝግጅት በማደርግበት ጊዜ የተረዳሁት ቁም ነገር፣ የሰውን ሸክም ማገዝ ማለት በልግስና፣ በቁሳዊ ነገሮች እና በምድራዊ ኑሮ ተግዳሮቶች አገዛ ላይ ብቻ የተመሠረተ አለመሆኑን ነው፡፡ ዋናው የሰው ሸክምም በዚህ ምድር ሕይወቱ ላይ የተወሰነ አይደለም፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፡፡ “ኃጢያቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሏልና፤ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዷልና፡፡” መዝ. 37(38) ኢየሱስ ክርስቶስም “ሸክማችሁ የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡” ይላል ኢየሱስ “ሸክማችሁ” በሚልበት ጊዜ ምድራዊ የኑሮ ተግዳሮቶቻችንን ማለቱ እዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ሸክሙ ኃጢያቱ ነው፡፡ አዳም ባለመታዘዙ የተጣለበት የኃጢያት ዕዳ ሸክም ሆኖበት ይኖር ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ በከፈለው የደም መስዋዕትነት ከሸክም አነጻው፡፡ መስቀሉን ተሸክሞ እየወደቀ እየተነሳ በከፈለው ህማም አዳም ቀና ብሎ እንዲሄድ አደረገው፡፡ የሰው ሸክሙ ኃጢያቱ ነው፡: ኃጢያት በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የሚጋርድ፣ ለሰው ቀንበር ሆኖ አንገቱን የሚያስደፋ ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰው ዘወትር በኃጢያቱ እየተጸጸተ ሊላቀቀው ቢመኝም፣ ትላንት በተገኘበት ነውር ዳግም እንዳይቆም ዘወትር በንስሐ ጊዜው ሁሉ ቁርጥ ፈቃድ ቢያደርግም፣ ተመልሶ እዛው ይገኛል፡፡ ስለዚህ መተጋገዝ እጅግ ያስፈልጋል፡፡ ጳውሎስ ይህንን መልዕክት ሲጽፍ ያሳሰበው ነገር የነበረ ይመስለኛል፡፡ እሱም ሰው በባሕሪው ራሱን ብርቱ ሌላውን ደካማ አድርጎ የሚመለከት የመሆኑ ነገር ነው፡፡ ኃጢያተኛን በሸክሙ ከማገዝ ይልቅ ጣት በመጠቋቆም በሸክሙ ላይ ሌላ ሸክም በመጨመር ጭንቀቱን ያባብስበታል፤ እንዳውም አንዳንዶቻችን “በእንደዚህ ያለ ኃጢያት ስላልተገኘሁ እግዚአብሔር ሆይ ተመስገን” በማለት የልበ ቢሱን ባለጸጋ ጸሎት እንደግማለን፡፡ ጳውሎስ የገላቲያ ሰዎች ከዚህ በመታቀብ በኃጢያቱ ያዘነ ሰው ባጋጠማቸው ጊዜ እንዲያግዙት፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲያስታውሱት እና በጸሎት እና ኃጢያትን በመጸየፍ እንዲኖር መንገድ እንዲያሳዩት ሊያሳስባቸው የፈለገ ይመስለኛል፡፡ ያዕቆብ በመልዕክቱ “ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው ኃጢያተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኃጢያትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ፡፡” ይላል፡፡ (ያዕ. 5፡19) ይህንንም ለማድረግ ሁላችን በተለያየ ኃጢያት የምንኖር መሆናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሌሎችን በኃጢያት ሸክማቸው እንድናግዛቸው ጥሪ የቀረበልን እኛ ከኃጢያት ነጻ ሆነን ስለ ተገኘን ሳይሆን በደካምነት ውስጥ ያለን ነገር ግን የእግዚአብሄርን ምሕረት የቀመስን በመሆናችን ነው፡፡ በመሆኑም በ1ኛ ቆሮ. 9፡22 ላይ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ እንደደካማ ሆንሁ፡፡ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደነሱ ሆንኩ፡፡” እንደሚለን ደካምነታችንን ሳንዘነጋ፣ ራሳችንን በሌሎች ሥፍራ በማኖር የቀመስነውን የእግዚአብሄርን ምሕረት እናጋራቸው፡፡ በኃጢያታቸው እጅግ ላዘኑት እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን እናስታውሳቸው፡፡ እንግዲህ ይህንን በማከናወናችን የኢየሱስን ሕግ እንፈጽማለን፡፡ ለመሆኑ የኢየሱስ ሕግ ምንድን ነው? የሙሴ ሕግ እንደምታውቁት “ለበደለኛ እንደበደሉ ይከፈለው” የሚል ነው፡፡ የኢየሱስ ሕግ ግን ከዚህ በፍፁም የተለየ ነው፡፡ “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፡፡” (ዮሐ. 15፡12) የኢየሱስ ሕግ ፍቅር ነው፡፡ ማንም በፍቅር ካልሆነ በስተቀር የሌላውን ሸክም ሊያግዝ አይችልም፡፡ የነገር ሁሉ መሠረቱ ፍቅር ነው፡፡ በኢየሱስ ሕግ መኖር እርሱንም መፈጸም ለእኛ ለክርስቲያኖች መለያችን ነው፡፡ የደቀ መዝሙርነታችን መለያ፡፡ ለመሆኑ ሸክማቸውን ልናግዛቸው የሚገቡ ሰዎች የሚገኙት የት ነው? ለክርስቲያኖች የነገር ሁሉ መጀመሪያቸው ቤታቸው ነው፡፡ በቤታችን ያሉ የቅርብ የኑሮ አጋሮቻችን፣ ባለቤታችን፣ ልጆቻችን፣ እኅት ወንድሞቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ በመሥሪያ ቤት አብረውን የሚሠሩ የሥራ ባልደረቦቻችን ሁሉ የኛ እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሸክማቸው ሸክማችን መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር መሐሪ የመሆኑን ምስክርነት ሌላ ሰው ሊመሰክርላቸው አይገባም፡፡ እኛ ዘወትር አጠገባቸው ያለን ሰዎች ልናበረታታቸው ይጠበቅብናል፡፡




Comments