top of page

መሸፈኛ 2

  • Feb 23
  • 2 min read

“… በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት”

ዘፍ. 6፡14

ሀብታሙ አብርደው በጡረ



ይህ  በመጻሕፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝና ብዙ ሰዎች ልብ ሳይሉት የሚያልፉት ምስጢር ነው። 

በዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር ኖኅን መርከቧን እንዲሰራ ሲያዘው፣ በውስጥም በውጭም በቅጥራን እንዲለቀልቃት ነግሮት ነበር። ቅጥራን ወፍራም ፈሳሽ የማሸጊያ ቁስ ሆኖ ውኃው ወደ መርርከቢቱ ውስጥ ሰርጎ እንዳይገባ የሚከላከል ነው። በመርከቢቱ ውስጥ ያሉት ሁሉ ከመጥፋት የዳኑት መርከቢቷ ውሃ የማታስገባ ሆና በመሠራቷ ጭምር ነበር ይህም በውስጥም በውጭም ከተለቀለቀችው ቅጥራን የተነሳ ነው። ከዚያም ከበርካታ ዓመታት በኋላ በዘጸአት መጽሐፍ ሕፃኑ ሙሴ በአባይ ወንዝ ላይ በትንሿ ቅርጫት ውስጥ በተቀመጠ ጊዜ፣ እናቱ ውኃው ወደ ቅርጫቱ ሰርጎ እንዳይገባ እና ህጻኑን እንዳይገድለው ቅርጫቷን በቅጥራን እንደለቀለቀቻት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሁለት እጅግ የተለያዩ ጊዜያት።  ነገር ግን ተመሳሳይ የመሸፈኛ ተግባራት። ይህ ተራ ግጥምጥሞሽ ከመሰለህ አስተውል።

በሁለቱም ታሪኮች ውስጥ፣ በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን የኖኅን ቤተሰቦችም ሆነ ህጻኑን ሙሴን ያዳናቸው የእንጨቱ ጥንካሬ አልነበረም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ያዘጋጀው መሸፈኛ እንጂ። መርከቧ ከጥፋት ውኃው በሰላም ያለፈችው፣ ሙሴም ከወንዙ የተረፈው በመሸፈኛው ምክንያት ነው። ደህንነታቸው ፈጽሞ በመርከቡ ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ አልነበረም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር መርከቡን ለማሸግ በተጠቀመበት በቅጥራኑ ላይ እንጂ። ይህ የመሸፈንና የመጠበቅ ተግባር በአዲስ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ከተፈጸመው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። 

ማናችንም ትጉህም ብርቱም ብንሆን በራሳችን ጽድቅ ለመቆም አንችልም። የሕይወት ጫናዎችን እየተቋቋምን ያለነውም ከግል ጥንካሪያችን የተነሳ ብቻ አይደለም። የቆላስይስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ሁሉ በእርሱ ጸንቶ ይቆማል ቆላ. 1፡17። የተወሰነው የሕይወታችን ክፍል ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገር በክርስቶስ ነው ጸንቶ የሚቆመው። ይህ ማለት ስሜትህ ሲናወጥ፣ ሕይወት ስትከብድህ፣ ወይም እምነትህ ሲላላ፣ ተስፋህ የተመሰረተው በአንተ የግል ጥረት እና ትጋት ላይ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እርሱን ደግፎ በሚይዘው በጌታ ኃይል ላይ ነው። እግዚአብሔር ኖህን በጥፋት ውኃ ውስጥ በታማኝነት እንደጠበቀውና ሙሴንም በወንዙ ውስጥ እንደተከላከለለት ሁሉ፣ ዛሬም በክርስቶስ በታማኝነት አንተን እና እኔን እየደገፈን ነው።

ይህ ማለት ሕይወት ፈጽሞ አይከብድም ፣ ማዕበል አይነሳም ማለትም አይደለም። ነገር ግን እነዚያን አውሎ ነፋሱንም ሆነ ወጀቡን ያለ መሸፈኛ ወይም ብቻህን አትጋፈጣቸውም ማለት ነው። እግዚአብሔር ራስህን ታጸና ዘንድ አይጠብቅብህም። በክርስቶስ በኩል እርሱ ራሱ በአንድነት አጽንቶ ይዞሃል።

ስለዚህ ሃሳቦችህ ከተበታተኑ፣ ወይም ሕይወት በዙሪያህ እንደሚነሳ ውኃ ሆና ከታየችህ፣ ረጋ በል፣ ወደ ራስህም ተመለስ፣ በረጅሙ ተንፍስና ይህንን እውነት አስታውስ። ኖኅን እና ሙሴን በተከለሉባቸው መሸፈኛዎች በኩል የጠበቀው ያው ታማኝ አምላክ፣ ዛሬም በልጁ በተፈጸመ የመስቀል ሥራ ሕይወትህን በግል እየደገፈ ያለ ጌታ ነው። ዝም ብለህ በውኃው ላይ ብቻህን እየቀዘፍክ እንደሆነ አታስብ። በክርስቶስ ሥጋ እና ደም፣ በአንድነት ተያይዘህ ጸንተህ ቆመሃል።


 
 
 

Comments


bottom of page