top of page

ወደ ጋብቻ ለመግባት ስናስብ ከሁሉ አስቀድመን ቦታ ልንሰጠው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?

  • Apr 21, 2016
  • 3 min read

Updated: Jan 11

ዛሬ እኛ ልንገባበት እና ቀሪ ዘመናችንን በቃል ኪዳን ልንመራበት የምንፈልገውን ጋብቻ የመሠረተው እና የቤተሰብ ሕይወት ደራሲ እግዚአብሄር ነው፡፡ ስለዚህ ያማክረን ዘንድ ወደ ጓደኛ፣ ዘመድ አዝማድ ወይም አማካሪ አና ባለሞያ ከመሄዳችን አስቀድመን በርከክ ነው ማለት ያለብን፡፡ ወደ አደግንባት፣ ምናልባትም ሕይወታችንን ሀ ብለን ወደጀመርንባት፣ ምናልባትም ደግሞ የመጀመሪያውን ምሥጢራት ወደተቀበልንባት ታቦት ሥር ድፍት ብለን የልባችንን ሀሳብ ከማንም በፊት ለእግዚአብሄር ማቅረብ ይገባናል፡፡ በጽሞና በፊቱ በቂ ጊዜ ማሳለፍ እጅግ ይጠቅመናል፡፡


የዛሬው ባለቤቴ በዛን ጊዜ አብሮኝ በአንድ ቁምስና በዝማሬ ያገለግል የነበረው የአገልግሎት የቅርብ ጓደኛዬ የፍቅር ግንኙነት እንድንጀምር ጥያቄ ያቀረበልኝ ዕለት መጀመሪያ ያደረግነው ነገር ቢኖር ምንም መልስ ሳንሰጣጥ ለአንድ ሳምንት በየግላችን በእግዚአብሔር ፊት ጉዳያችንን እንድናቀርብ መስማማት ነበር፡፡ ተስማምተን ብቻም አልቀረንም የያዝነው ጉዳይ በቀሪ ሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነውና ለአንዲት ቀን እንኳን ሳናጓድል ለጸሎት በወሰንናቸው ሰዓታት በየግላችን በእግዚአብሔር ፊት አሳለፍን፡፡


እነዚያ በእግዚአብሔር ፊት ያሳለፍናቸው ሰዓታት በሕይወታችን ሁሉ ሲከተሉን እና ሲጠብቁን ኖረዋል፡፡ ከበርካታ የዚህች ዓለም የትዳር ተግዳሮቶችም መንጥቀው አውጥተውናል፡፡ ስለዚህ ከማንም እና ከምንም በፊት እግዚአብሔርን አስቀድሙ፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ከሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀው ወደ ትዳር ለመግባት የሚወስኑት ውሳኔ ነው፡፡ ወደ ትዳር ለመግባት ደግሞ ትዳርን ከስር ከመሠረቱ ከጠነሰሰው ከግንኙነቱ ባለቤት ከእግዚአብሔር የበለጠ አማካሪ ሊኖረን አይችልም፡፡ ስለዚህ ቁጥር አንድ እግዚአብሔር፡፡


ቁጥር ሁለት ወደ ትዳር ለመግባት የወሰንንበት የዕድሜ ክልል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ባልበሰለ ዕድሜ የምንመሠርተው ጋብቻ ባብዛኛው ውጤቱ አሳዛኝ ሆኖ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ ከመጠናቀቅ ቢተርፍ እንኳን ትዳሩን አጽንቶ ለማቆየት የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ የትዳር ሕይወት ውስጥ የገጠሙን፣ ዛሬ በእግዚአብሔር ፀጋ እንደታሪክ የምናነሳቸው እና በወቅቱ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈሉን ተግዳሮቶች ያስተማሩን እውነት ነው፡፡ ያየነውን ጥሩ የሚመስል ነገር ሁሉ ለመሞከር፣ ቆንጆ ሆነን ለመታየት፣ ለመዝናናት እና ለሕይወታችን መሠረታዊ እና አስፈላጊ ላልሆኑ ሌሎች ነገሮች ቅድሚያ በምንሰጥበት ዕድሜ የምንመሠርተው ጋብቻ አብሮነታንን እጅግ ይፈታተነዋል፡፡ በሰል ብለን ማስተዋል እና መረጋጋት በምንጀምርበት ዕድሜ የተሸለ መታገስ እና የሌላውን ሰው ስሜት በተሸለ ሁኔታ መረዳት፣ ስለምንችል በዚህ ጊዜ ትዳር ብንመሠርት ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ይሆናል፡፡


ቁጥር ሦስት የትዳር አጋራችንን ለመምረጥ የምንወስደው ጥንቃቄ ነው፡፡ ወደ ትዳር ለመግባት ከምንጓዛቸው መንገዶች ወሳኝ ከሆኑ ደረጃዎች አንዱ ይሔኛው ነው፡፡ ስኬታማ ትዳር እንዲኖረን ለእግዚአብሔር ከምናቀርበው ጸሎት በተጨማሪ የእኛም ተሣትፎ አስፈላጊ ነው፡፡ የትዳር ጓደኛ ምርጫችንን በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል፡፡ በመጀመሪያ ቀደም ሲል እንደተነጋገርነው የምርጫችንን ኃላፊነት በጸሎት ለእግዚአብሔር አሳልፈን መስጠት አለብን፡፡ ለአዳም ሔዋንን የሠራለት እግዚአብሔር ነው፡፡ ልብ በሉ አዳም እንዲሠራለት አልጠየቀውም፡፡ ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም ሆኖ ያልታየው እግዚአብሔር እራሱ ነው ሔዋንን የሠራለት፡፡ ስለዚህ ለእናንተም የሔዋናችሁ ጉዳይ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ ይህንን በእግዚአብሔር እጅ የሚገኝ ጉዳያችንን ለመቀበል በጸሎት በፊቱ መቅረብ ይገባናል፡፡ ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ምርጫ ሆኖ በቀረበላችሁ የትዳር አጋር ላይ መሥራት፣ መቀራረብ፣ መተዋወቅ አልፎ ተርፎም ዓመል ለዓመል መተራረቅ የሰው ሥራ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጸሎት እና በእግዚአብሔር ድጋፍ ነው ይህም የሚሆነው፡፡


ቁጥር አራት በፍቅር ጓደኝነት የምናሳልፈው በቂ ጊዜ ነው፡፡ ተጠዳድፎ ወደ ትዳር ሕይወት መግባት የሚመከር አይደለም፡፡ በፍቅር ጓደኝነት በቂ ጊዜ ማሳለፉ የበለጠ መተዋወቅ እንድንችል ይረዳናል፡፡ ይህም በኋላ በትዳር ውስጥ የሚጠብቀንን የቤት ሥራ ያቃልልልናል፡፡ አንዳችን ለሌላችን ያለንን አክብሮት፣ ፍቅር፣ ቀረቤታ በመጨመር ቅድሚያ የመሰጣጠት ሁኔታን የበለጠ ለመለማመድ ዕድል ይሰጠናል፡፡

ቁጥር አምስት ትዳር ለመመሥረት የፈለግንበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? ብቸኝነትን ለመሸሽ፣ ቤተሰብ ጓደኛ “ለምን አታገባም/ቢም? እያሉ የሚወተውቱንን ውትወታ ለማምለጥ ወይንም በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ተማርከን የምንመሠርተው ትዳር ጤናማ እና ዘላቂነቱ እጅግ የመነመነ ነው፡፡


ቁጥር ስድስት በአሜሪካ የተደረገ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንዳረጋገጠው ተጋቢዎች ከተመሳሳይ የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታ የተገኙ እና የእውቀት ደረጃቸው ብዙ ያልተራራቀ መሆኑ በትዳር ተግባብተው ለመቆየት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ተመሳሳይ የጀርባ ታሪክ ያለን በሚሆን ጊዜ የቤት ሥራችን ቀላል ይሆንልናል፡፡


በሀሳብ መቀራረብን ማዳበር እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ተቃራኒ ሀሳብ ይዘን መገኘት ያስደስተን ይሆናል፡፡ በትዳር ሕይወት ውስጥ ለስኬታማ ሕይወት የሚረዳን ሀሳብን በመቀባበል መረዳዳትን መለማመዱ ነው፡፡


ቁጥር ሰባት መልካም ባሕሪን ማዳበር ነው፡፡ መልካም ባሕሪ ያዳበረ ሰው ለእያንዳንዱ ጉዳይ ኃላፊት የተሞላው ውይይት ያደርጋል፡፡ መልካም ባሕሪ ያላቸው ሰዎች የሚፈጽሟት እያንዳንዷ ነገር በትዳራቸው ላይ የምታሳርፈውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለይተው ያውቃሉ፡፡ በመሆኑም በትዳራቸው ላይ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሚገባ ይወጣሉ፡፡


ቁጥር ስምንት በወላጆቻችን ትዳር ላይ የነበረው የስኬታማነት ሁኔታ በእኛ ሕይወት ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ነው፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት በፍቺ ምክንያት ከፈረሱ ቤተሰቦች የሚገኙ ባለትዳሮች ተመሳሳይ ሁኔታ ሊገጥማቸው የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጧቸው እና በቅርብ የሚያውቋቸው ቤተሰቦቻቸው ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት እና ጋብቻቸውን ከመፍረስ ለመታደግ ሳይችሉ መቅረታቸውን ስለሚያውቁ ነው፡፡ እነርሱም በትዳር ሕይወታቸው ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች እና የሀሳብ ልዩነቶች ፍቺን እንደ መፍትሔ አድርገው ሊወስዱ ይችላሉ፡፡


ቁጥር ዘጠኝ ወላጆቻችን በትዳራችን ላይ ያላቸው አመለካከት የሚፈጥረው ተጽዕኖ ነው፡፡ ወላጆቻችን ጋብቻችን የማይረባ እና ምንም ዓይነት ዋስትና አንደሌለው በሚያስቡ ጊዜ ይህ አመለካከተቻው በእኛ የትዳር ሕይወት ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ በትዳራችን ውስጥ በቀላሉ ልንግባባቸው የምንችላቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እንኳን ሳይቀር “ድሮም ቢሆን” በሚል አጭር አስተሳሰብ ራሳቸውን ለውይይት ዝግ ያደርጋሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወላጆች በመልካም አመለካከት እና ምክር የሚደግፉት ትዳር እርስ በእርስ ለመከባበር እና ለመደማመጥ ያለው ዕድል ሰፊ ነው፡፡


ቁጥር አስር ለፆታዊ ግንኙነት ተገቢውን ኃላፊነት መወጣት ነው፡፡ በፆታዊ ግንኙነት ላይ ያለን አመለካከት መከባበርን እና አንዱ የሌላውን ውሳኔ በመደገፍ ላይ የተመሠረተ መሆን ይገባዋል፡፡ የፆታዊ ግንኙነት ኃላፊነቶች የጋራ ናቸው፡፡ በግልጽ በመወያየት አንዳችን ለሌላችን ደስታ፣ ምቾት ቅድሚያ በመስጠት፣ በመተሳሰብ, በመተማመን፣ እና በግልጽ በመነጋገር ላይ የተመሠረተ በሚሆንበት ጊዜ በትዳራችን ጤናማነት እና ስኬታማነት ላይ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡


ቸር ይግጠመን

 
 
 

Comments


bottom of page