የጋብቻ ቀለበታችንን በግራ እጃችን የምናደርገው ለምንድ ነው?
- Apr 21, 2016
- 3 min read
Updated: Jan 11
የጋብቻ ቀለበታችንን በግራ እጃችን የምናደርገው ለምንድ ነው?
የቀለበት ጣታችንስ ለምን ተመረጠ?
ዛሬ በጥቂት የዓለማችን ክፍል ካልሆነ በስተቀር የጋብቻ ቀለበት የሚደረገው በግራ እጅ የቀለበት ጣት ላይ ነው፡፡ በርካታ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶችም ይህንኑ ተግባራዊ እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለመሆኑ ይህ የጋብቻ ቀለበትን በግራ እጅ የቀለበት ጣት ላይ የማጥለቅ ልማድ የተገኘው ከየት ነው? መሠረታዊ እምነቱስ ምንድን ነው?
የጋብቻ ቃል ኪዳንን በማስመልከት በጣት ላይ ቀለበት ማድረግ የተጀመረው በጥንት ግብጻውያን ዘመን መሆኑን ታሪክ ይናገራል፡፡ ይኸውም ከክርስቶስ ልደት 3000 ዓመታት አስቀድሞ መሆኑ ነው፡፡ ጥንታውያን ግብጻውያን በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ የበቀሉ ቄጤማዎችን በመጎንጎን በጣታቸው ላይ እንደ ቀለበት፣ በእጃቸውም ላይ እንደ አምባር በማሰር እና የጋቻ ቃል ኪዳን ማመላከቻ በማድረግ ይጠቀሙበት ነበር፡፡
በዚያን ዘመን በነበረው የግብጻውያን ሥልጣኔ አስተሳሰብ በሰው ልጆች የግራ እጅ ላይ ከሚገኘው የቀለበት ጣት ተነስቶ በቀጥታ ወደ ልብ የሚጓዝ አንድ ትልቅ የደም ሥር (የፍቅር ሥር) አለ ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ከዚህም በመነሣት የጋብቻ ትሥሥር ልባዊ ፍቅርን መሠረት ያደረገ መሆኑን ለማመልከት ግብጻውያኑ ከቄጤማ በመጎንጎን ያበጇቸውን ቀለበቶች በግራ እጃቸው የቀለበት ጣት ላይ ያጠልቁ ነበር፡፡
በኋላ ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት 332 ዓ.ዓ. አካባቢ ግሪካውያን በግብጽ ላይ በተቀዳጁት የበላይነት የተነሣ ይህንን እምነት ወደ ግሪክ በመውሰድ ማዘውተር እንደጀመሩ ታሪክ ይዘግባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በዘመኑ ታላቅ ግዛት ወደነበረችው ወደ ሮማ በመዛመት ምእራባውያን ዘንድ በመድረሱ በመላው ዓለም የተሠራጨ እምነት ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡
በእርግጥ በዘመናችን ሣይንስ የተጠቀሰው የደም ሥር በግራ እጃችን የቀለበት ጣት ላይ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ባይሰጥበትም እጅግ በርካታ ክፍለ ዘመናትን ተሸግሮ ዛሬም ድረስ ሰፊውን የዓለም ክፍል ያዳረሰ ተግባር ሆኖ ቀርቷል፡፡
ስለ ጋብቻ ቀለበት ካነሣን አይቀር የቀለበቱ ቅርጽ እና ባብዛኛው ከወርቅ የተሰራ እንዲሆን መፈለጉ ምን ትርጓሜ እንዳለው እንመልከት፡፡ የጋብቻ ቀለበቱ በክብ የተሠራ መሆኑ የሚያመለክተው በተጋቢዎች መካከል የተመሠረተው ጥምረት የማይቋረጥ እና ዘለዓለማዊ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ጣት እንዲጠልቅበት የሚዘጋጀው ቀዳዳ ደግሞ ተጋቢዎቹ የሚገቡበትን አዲስ ዓለም መግቢያ በር የሚወክል ሲሆን በሚገቡበት ዓለም ወደ ሚያጋጥማቸው የሚታወቅም ሆነ የማይታወቅ ዕጣ ፈንታ የሚያሸጋግር በር ነው፡፡
ቀለበቱ በተቻለ መጠን ከወርቅ እንዲሠራ የሚፈለገው በሁለቱ መካከል ራሥን በሙላት ለሌላው በማቅረብ የሚደረገው ቃልኪዳን እጅግ ዋጋ ያለው ሥጦታ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁላችንም እንደምናውቀው ወርቅ፣ ወርቅ መሆኑን ለመለየት እና ያለውን ውበት እና ተወዳጅነት ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያልፍባቸው እጅግ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እንግዲህ በዚህኛውም ሆነ በሚመጣው ዓለም ከእሳት የከፋ ፈተና የለም፡፡ ወርቅም ወርቅነቱን ለማረጋገጥ በእሳት መለብለብ፣ በአሲድ መነከር እና እጅግ ሹል በሆኑ የሽቦ ጥርሶች መፈተግ አለበት፡፡ ወርቅ በእነዚህ ሁሉ ፈታኝ ጎዳናዎች አልፎ ነው አብረቅርቆ የምንመለከተው፡፡ ስለዚህ ተጋቢዎቹም የሚገቡት ቃልኪዳን በእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ ጸንቶ የሚያልፍ መሆኑን እና በዚህም አብረቅራቂ የወንጌል ምሥክሮች መሆናቸውን ለማረጋገጥ የወርቅ ቀለበት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡
የጋብቻ ቀለበትን ለምን በቀለበት ጣታችን ላይ እንደምናደርግ ከሚሰጡ መላምቶች መካከል ለእኔ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠኝ በቻይናውያን ዘንድ የሚገለጸው ማብራሪያ ነው፡፡ ላካፍላችሁ፡፡
አምስቱ ጣቶቻችን የሚወክሉት የተለያዩ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሰዎች ነው፡፡ የአውራ ጣቶቻችን ወላጆቻችንን፣ አመልካች ጣቶቻችን እኅት፣ ወንድም እና ሌሎች የቤተዘመድ አባላትን፣ የመካከል ጣታችን ራሳችንን፣ የቀለበት ጣታችን ወደፊት በሕይወታችን የትዳር አጋራችን እንዲሆን/ድትሆን እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ልጅ ሲሆን ትሿ ጣታችን ደግሞ ልጆቻችንን ትወክላለች፡፡
እስኪ የሁለቱንም እጆቻችሁን ጣቶች እርስ በእርስ ጫፎቻቸውን አገናኟቸው፣ አውራ ጣትን ከአውራ ጣት፣ አመልካች ጣትን ከአመልካች፣ እንደዚያ እያደረግን ሁሉንም እናገናኛቸው፡፡ በጣቶቻችን እንደማጨብጨብ እያደረግን ሁሉንም ጣቶቻችንን በቀላሉ እያለያየን ማገናኘት እንችላለን አይደል? ነገር ግን ትዳር ከመሠረትን በኋላ የግራ እጃችን የቀለበት ጣት የትዳር ጓደኛችንን የሚወክል ሲሆን የቀኝ እጃችን የቀለበት ጣት ደግሞ እኛን ይወክላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ትዳር ከመመሥረታችን አስቀድሞ እኛን ይወክል የነበረው የመካከል ጣታችን አያስፈልግም ማለት ነው፡፡ ሁለት እኛነት የለምና፡፡ ስለዚህ መሞት እና መቀበር አለበት፡፡ ትዳር ከመሠረትን በኋላ የምንኖረው በአዲሱ የጋራ ማንነታችን እንጂ በቀደመው የግል ማንነታችን አይደለም፡፡ የቀደመው የግል ማንነታችን መሞቱን እና መቀበሩን ለማመልከት ሌሎቹ ጣቶቻችን እንደተነካኩ ሁለቱን የመካከል ጣቶቻችንን ብቻ በማጠፍ ዝቅ እናድርጋቸው፡፡
አሁን እስኪ የመካከል ጣታችን እንደታጠፈ እንደቅድሙ ወላጆቻችንን በሚወክሉት በአውራ ጣቶቻችን ወይም እኅት ወንድሞቻችንን እና ቤተዘመዶቻችንን በሚወክሉት የአመልካች ጣቶቻችን ለማጨብጨብ እንሞክር፡፡ በቀላሉ እየተላያዩ ተመልሰው መግጠም ይችላሉ አይደል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ወላጆቻችንም ሆነ ቤተዘመዶቻችን አብረውን የሚኖሩት ለተወሰነ ጊዜ መሆኑንና ራሳችንን በቻልን ጊዜ ከእነርሱ ተለይተን የራሳችንን ሕይወት እንደምንጀምር ነው፡፡ ልጆቻችንን የሚወክሉትን ትናንሽ ጣቶቻችንን ለማለያየት ብንሞክርስ ይቻላል? አዎን በቀላሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተው ልጆቻችንም ቢሆኑ ከእኛ ጋር የሚኖሩት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ራሳቸውን ሲችሉ እኛን ወላጆቻቸውን ትተው የራሳቸውን ሕይወት ይመሠርታሉ፡፡ ማን ቀረ ታዲያ የቀለበት ጣቶቻችን፡፡ አይደል? እስኪ እነርሱን ለማለያየት ሞክሩ፡፡ ይቻላል? ፈጽሞ አይቻልም፡፡ አንድ ጊዜ በቃል ኪዳን ተሳስረናል እና እስፍጻሜው አብረን እንኖራለን፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ገድለን የቀበርነው ግላዊ ማንነታችንን ከተቀበረበት እንዲያንሠራራ ከፈቀድነለት (የመካከል ጣታችንን ካጠፍንበት ቦታ ቀና ለማድረግ ከሞከርን) የቀለበት ጣቶቻችን በቀላሉ ይለያያሉ፡፡ ስለዚህ ግላዊ ማንነታችንን የሚወክለው የመካከል ጣታችን በተቀበረበት ቦታ መቆየት ይኖርበታል፡፡
አይደላም?
ቸር ይግጠመን





Comments